በአማራ ክልል ከ7000 በላይ እስረኞች ከማረሚያ ቤት አምልጠዋል ተባለ

አማራ ክልል ዉስጥ እየተደረገ ባለ ውጊያ ምክንያት ከ 7000 በላይ እስረኞች ከማረሚያ ቤት አምልጠዋል ተብሏል።

ከአመለጡት መካከል አንዳንዶቹ በተጠቂዎች መገደላቸዉ ሲገለፅ ሌሎቹ ደግሞ ከሳሾቻቸዉ ላይ ጉዳት ማድረሳቸዉ ተነግሯል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት እንዳስታወቀው በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከአሥር ማረሚያ ቤቶች ሰባት ሺሕ ታራሚዎች መበተናቸውን ገልጿል፡፡

በምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔ ላይ እንደተገለጸው በክልሉ በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት ከተበተኑበት ተይዘው የተመለሱት በጣም አነስተኛ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ባለው ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ላይ የሚደረገው ቁጥጥር በታቀደው ልክ አለመሳካቱን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በሚታየው የፀጥታ ችግር የሕዝቡ ነፃ እንቅስቃሴ በሰፊው የተገደበ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን ግድያ፣ ዝርፊያ፣ ዕገታ፣ የዜጎች እንግልት፣ ከእሴትና ከባህል ያፈነገጡ የጭካኔ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው ብለዋል፡፡

የክልሉን የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ ይበልጥ እያወሳሰበ ያለው ምክንያት፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት መጣስ፣ የማንነትና የወሰን ጥያቄ ባሉባቸው የክልሉ አካባቢዎች ሕገወጥ አማራጮችን በማስቀደም አሁንም በሕዝብ ላይ ወንጀሎች እየተፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት በግልጽ የተቀመጡ ግዴታዎች እንዲፈጸሙ እንዲደረግና በወንጀል ድርጊት ተሳታፊዎች ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ የማንነትና የወሰን ጥያቄ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ብቻ መፍትሔ እንዲያገኝ አጽንኦት ተደርጎ መሠራት ይኖርበታልም ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ወቅታዊ የፀጥታ ችግርን ላልተገባ ዓላማ ለማዋል የሚሞክሩ ግለሰቦች በመኖራቸው፣ በዚህም ምክንያት በቂም በቀል ለጉዳት በሚዳረጉ ግለሰቦች ምክንያት ሁኔታውን ላልተገባ ጥቅም ማካበቻ የሚያደርጉ አካላት እንዳሉም ተገልጿል፡፡

እንዲሁም ያለ ፍርድ ለረዥም ጊዜ በጊዜያዊ ማቆያ ያሉ ሰዎች አያያዝ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና ችግሩን ገምግሞ ፈጣን ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በጉባኤው ለይ ተገልጿል፡፡

በአማራ ክልል ያለው ጦርነት ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ከ6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርታቸው አቋርጠዋል፡፡

በርካታ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ መካከል የሚደረገው ጦርነት እንዲቆም እና ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *