የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች አሠሪ ፌዴሬሽን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመዋል፡፡
ስምምነቱ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች አሠሪ ፌዴሬሽን በውጭ ሀገር በሥራ የሚሰማሩ ዜጎችን መብት እና ደህንነት ለማስጠበቅ ያለመ ነው፡፡
በስምምነቱ ወቅት የፌዴሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ፣የዓለም ሥራ ድርጅት ተወካይ እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ በፊርማው ሥነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ኮንፌዴሬሽኑ በሀገር ውስጥ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች መብቶች እንዲከበሩ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከሀገር ውስጥ በተጨማሪም በውጭ ሀገራት ተቀጥረው የሚሠሩ ኢትዮጵያዊን መብታቸው ተጠብቆ እዲሠሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፤
ከኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች ፌዴሬሽን ጋር በጋራ ለመሥራት በርካታ ጥረት ሲደረግ የነበረ መሆኑን አንዱ ማሳያ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ይህ የመግባቢያ ሰነድ ወደ ትግበራ ሲገባ በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት የሚሰማሩ ዜጎች ከምልመላ ጀምሮ እስከሚሄዱበት የመዳረሻ ሀገራት እና ቆይታቸው ላይ በጋራ በሚመሰረተው የቅጥር እና የምልመላ አማካሪ ኮሚቴ (Migrant Workers Recruitment Advisory Committee) አማካኝነት መረጃዎችን በመሰብሰብ እና ልውውጥ በማድረግ የዜጎችን መብት እንደሚያስከብር ገልፀዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ ከኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች አሠሪ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ መሥራታቸው በርካታ ዜጎች ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲሰማሩ ከማገዝ በተጨማሪ ዜጎች ላይየሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈፀምባቸው ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ካሳሁን ፎሎ ሠራተኞችን በማኅበር የማደራጀት ሥራ የኢሠማኮ እንደመሆኑ በውጭ ሀገራት ያሉ ሠራተኞችም መደራጀት እንደሚያስፈልጋቸው፣ይህም ሠራተኞቹ የት እንዳሉ ለማወቅ ስለሚያስችል ጉዳት ሲደርስባቸው ክትትል በማድረግ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣም አረጋግጠዋል፡፡
ኢሠማኮ በውጭ ሀገራት ተቀጥረው የሚሠሩ ዜጎች መብት እንዲከበር ዓለም አቀፍ ከሆኑ አቻ ማኅበራት ጋር ጭምር የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈራረም በጋራ እየሠራ እንደሚገኝም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡
ኢሰማኮ ከዚህ በፊት ከሊባኖስ ሠራተኛ ማኅበር ጋር እና ከኩዌት የሠራተኛ ማኅበራት ፌዴሬሽን ጋር የሰራተኞችን ደህንነት ለማስከበር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙንም ገልጸዋል፡፡
ከነዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ከሀገር ሲወጡ ቅርብ ያሉ ሀገራትን አቋርጠው ስለሚሄዱ በመተላለፊያ የሚገጥማቸውን ችግር ለመቀነስ ከተቻለም ለማስቀረት ከደቡብ ሱዳን እና ከሶማሊያ ሠራተኛ ፌዴሬሽን ጋርም ተፈራርሟል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ነቢል መሀመድ በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት በሥራ የሚሰማሩ ዜጎች መብት፣ ክብር እና ደህንነት እንዲጠበቅ ለኤጀንሲዎች ከመንግስትና ከአለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) ጋር በመተባበር በርካታ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ኩዌት፣ ሊባኖስ፣ ባህሬን ፣ ኳታር እና ኦማን ኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች በብዛት የተቀጠሩባቸው ሀገራት ናቸው፡፡