የቀድሞ አትሌቶች በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ላይ ክስ አቀረቡ

የኢትዮጵያ ቦክስ እና ቴኒስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እና አትሌት ገዛኸኝ አበራ በጋራ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ላይ ክስ መስርተዋል።

ክስ ከተመሰረተባቸው አመራሮች መካከል የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ፣ የኮሚቴው ዐቃቤ ነዋይዋ ዶ/ር ኤደን አሸናፊ ፣ ዋና ፀሐፊው አቶ ዳዊት አስፋው እና ምክትል ፀሐፊው አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ዋነኞቹ ናቸው።

ክሱን ተከትሎም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሁሉም የባንክ አካውንቶች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋልም ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ክስ እንደቀረበባቸውም ይፋ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና በዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ላይ ከተመሰረቱ ክሶች መካከል :- ባልተገባ መልኩ የሰው ዝውውር በማድረግ፣ ኦዲት ያልተደረገ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በካሽ እና በአይነት መኖሩ፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከ64 ሚልዮን ብር በላይ የሚያወጣ ፋብሪካ እገነባለሁ ብሎ የተገዙት ማሽኖች የት እንዳሉ አለመታወቃቸው ዋነኞቹ ናቸው።

እንዲሁም በፓሪሱ ኦሊምፒክ ወደ ፈረንሳይ ተጉዘው የቀሩ እና የመጡ ግለሰቦች በምን መመዘኛ ወደ ስፍራው እንደተጓዙ፣ ሁለቱ የኦሊምፒክ አመራሮች ለሶስተኛ ግዜ የኢትዮጵያ ዜግነት ሳይኖራቸው መመረጣቸውን ከቀረቡ ክሶች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ በተቋሙ እና አመራሮች ላይ የቀረቡ ክሶች ሀገርን ለማስቀጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ በመሆኑ ክሱ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ብሏል፡፡

በፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፍርድ ቤት የቀረበበትን ክስ ተከትሎ ይፋዊ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በተሰጠው ስልጣን እና ተግባር መሰረት ሀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኮሚቴው በመግለጫው ይሁን እንጂ በተቋሙ አሰራር የሚደሰት እና ቅሬታ ያለው ይኖራል ይህም ተፈጥሯዊ ነው“ ያለ ሲሆን ተቋሙ በስፖርት መድረክ አለመግባባቶች እና ቅራኔዎች ሲኖሩ የሚስተናገዱበት መንገድ  በመተዳደሪያ ደንቡ በግልፅ ተቀምጧል ብሏል፡፡

የኦሎምፒክ ኮሚቴው ማናቸውም ቅራኔዎች ወይም ከስፖርት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሲያጋጥሙት ከመደበኛ ፍርድ ቤት ውጪ ለችግር አፈታት በሚቋቋም የፍትህ አካል እንደሚፈታ ገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *