ዘጠኝ ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ህጻናት ከትምህርት ገባታ ውጭ መሆናቸው ተገለጸ

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ 8 ነጥብ 85 ሚሊየን ህጻናት በትምህርት ገበታ ላይ አይገኙም ብሏል።

የሀገሪቱ የትምህርት ሁኔታ አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛል ያለው ዩኒሴፍ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በሀገሪቱ በበርካታ ቦታዎች እየተባባሰ የመጣው ግጭት ነው ሲል ጠቁሟል።

በተያዘው የፈረንጆቹ አመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት (ጥር፣ የካቲትና መጋቢት) በሀገሪቱ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች ቁጥር በ18 በመቶ ጨምሯል ያለው ዩኒሴፍ ጉዳት የደረሰባቸው የትምህርት ቤቶችን ቁጥር በ5 ነጥብ 5 በመቶ መጨመሩንም ጠቁሟል።

በሀገሪቱ 6 ሺ 770 ትምህርት ቤቶች ጉዳት ሲደርስባቸው 6 ሺ 410 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ተዘግተዋል ሲል በየሶስት ወሩ በትምህር ዙሪያ በሚያሳትመው ኒውስሌተር ላይ ባሰፈረው ሪፖርት አስታውቋል።

በትምህርት ገበታ ላይ የማይገኙ የሀገሪቱ ህጻናት ቁጥር (out-of-school children or OOSC) በአስደንጋጭ ሁኔታ ከ2023 አጋማሽ ጀምሮ እየጨመረ ይገኛል ብሏል።

በኢትዮጵያ ድርቅ እና ጎርፍ የትምህርት ሂደቱን በማደናቀፍ ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚሄዱ ህጻናት ቁጥርን እንዲቀንስ እንደሚያደርግ የጠቆመው ዩኒሴፍ ከመጋቢት ወር ወዲህ ብቻ አንድ ሚሊየን ህጻናት በድርቅ ሳቢያ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳይሄዱ ማድረጉን ተቋሙ አስታውቋል፡፡

ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጦርነት እየተካሄደ ባለበት የአማራ ክልል ውስጥ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንዳሉት በጦርነቱ ምክንያት ከ1 ሺህ 200 በላይ በኾኑ ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ከስድስት ሺሕ በላይ ሠራተኞች ከሥራ ገበታ ውጭ ሆነዋል ብለዋል፡፡

የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊና የኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በዚህ ጦርነት ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከ15 ቢሊዮን በላይ ብር የሚያወጣ ንብረት ወድሟል ብለዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ በክልሉ በተከሰተዉ ጦርነት 298 ትምህርት ቤቶች በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ውጪ ሲሆኑ 3725 ትምህርት ቤቶች ደግሞ እንደተዘጉ ሃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል መናገሻ ባህር ዳር ንጹሃንን ከህግ አግባብ ውጪ ገድሏል ሲል ከሷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *