ኢትዮጵያ አዲስ የነዳጅ ማደያ ፈቃድ መስጠት አቆመች

በመላው ሃገሪቱ የነዳጅ ማደያ ፍቃድ ላልተወሰነ ጊዜ መታገዱ ተገለጿል፡፡

የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን አሁን ላይ የነዳጅ ማደያ ማስፋፊያ ፍቃድ ሙሉ ለሙሉ አስታውቋል፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ እንደተናገሩት መንግስት የነዳጅ ማደያ ማስፋፊያን የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

መንግስት የነዳጅ ማደያዎችን በሀገር ውስጥ ለማስፋፋት በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ አሁን ላይ ግን ባልተፈለገ አቅጣጫ እየሄደ መሆኑን ባለስልጣኑ በማረጋገጡ ፍቃዱ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታገድ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ባለስልጣኑ ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት ወ/ሮ ሳህረላህ የማደያዎች ፍቃድ አሰጣጥ እና ተደራሽነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ ካገኙ በኋላ ፍቃድ የመስጠቱ ስራ ዳግም እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

ችግሩ ከተፈታ በኋላ በተለይም የነዳጅ ማደያ ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች በስፋት የሚሰራ ይሆናልም ብለዋል፡፡          

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላህ አብዱላሂ የነዳጅ ማደያ ፍቃድ አሰጣጥ ብዙ ጥናት ማድረግን የሚፈልግ ስራ በመሆኑ መቼ ይጀምራል የሚለውን ጥያቄ ግን ሳይመልሱ ቀርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለነዳጅ ግዢ አራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአንድ ወር በፊት ከታማኝ ግብር ከፋዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ በየዓመቱ አራት ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ግዢ ማውጣት እንደማትችል ገልጸው ባለሀብቶች በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን እንዲያስመጡ እና በሀገር ውስጥ መገጣጠም እንዲጀምሩ መንግስትም ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ሙሉ ለሙሉ ያገደች ሲሆን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እንዲያስገቡ ወይም በሀገር ውስጥ እንዲገጣጥሙ እስከ 35 በመቶ የግብር ቅናሽ እንደሚደረግላቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የየነዳጅ ፍላጎቷን ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ሀገራት በመግዛት የምትሸፍን ሲሆን የትራንስፖርት ዋጋ እንዳያንር በሚል የነዳጅ ድጎማ ስታደርግ ቆይታለች፡፡

የመንግስት ወጪ በመጨመሩ እና የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት የነዳጅ ድጎማን ቀስ በቀስ ለመቀነስ እና ለማቆም እንደወሰነች የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባሳለፍነው ዓመት ይፋ አድርጓል፡፡

የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለማይሰጡ ድርጅቶች የነዳጅ ድጎማው ከቆመ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን አሁን ደግሞ የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችም የነዳጅ ድጎማ እንደማያገኙ ተገልጿል፡፡

ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የነዳጅ ድጎማ ሲደረግላቸው የነበሩ የሚኒባስ ተሽከርካሪዎች ከመጋቢት 30 ቀን  2016 ዓ.ም ጀምሮ ድጎማው እንደሚቋረጥ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታውቋል።

መንግሥት ለረጅም ጊዜ ለነዳጅ ምርቶች ከፍተኛ መጠን የለው ድጎማን ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጽ ይህንን ለማስቀረት በሂደት የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ባወጣው ዕቅድ መሠረት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ቀስ በቀስም መንግስት በነዳጅ ምርት ላይ የሚያደርገዉ ድጎማ የማቋረጥ እቅድ እንዳለዉ ይታወቃል፡፡

በሚኒባስ ተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረገዉ መንግስት ድጎማን የማስቀረቱ አንዱ አቅድ መሆኑ ተመላክቷል፡፡  ሆኖም የድጎማ ስርአቱን የሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎች ማህበረሰቡን በሚገባ እያገለገሉ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሰልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሄኖስ ወርቁ ከዚህ ቀደም 170ሺ ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ስርአት ውጪ መደረጋቸዉን ተናግረዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *