ኢትዮጵያ እና ዓለም ባንክ የ1 ነጥብ 72 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ97 ቢሊዮን ብር እርዳታ እና በድር ስምምነት መፈራረማቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ እና በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ተወካይ የሆኑት ኦስማን ዲዮን ተፈራርመዋል ተብሏል፡፡
ከዓለም ባንክ ከተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ 850 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ በእርዳታ ለኢትዮጵያ የተለያዩ ስራዎችን ለመደገፍ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
ቀሪው ገንዘብ ደግሞ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት እና ለማከናወን በሚል በብድር መልኩ ከባንኩ እንደተሰጠ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
በእርዳታ ከተሰጠው ገንዘብ ውስጥ 500 ሚሊዮን ዶላሩ ለገጠር አካባቢዎች የምግብ ዋስትና፣ የአየር ንብረት ለውጥ ስራዎችን ለመደገፍ፣ 82 ዶላሩ ደግሞ በከተማ አካባቢዎች ምግብ ዋስትና ስራዎችን ለማረጋገጥ ይውላል ተብሏል፡፡
እንዲሁም 340 ሚሊዮን ዶላሩ በቆላማ አካባቢዎች ያሉ ዜጎችን ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥ ስራዎችን ለመደገፍ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
ቀሪው 275 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ በከተሞች አካባቢ ያሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚውልም ተገልጿል፡፡
የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች ቡድን በአዲስ አበባ ለሁለት ሳምንታት ከኢትዮጵያ በለስልጣናት ጋር ሲመክር ቆይቶ መመለሱ ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት ወደ አዲ አበባ የመጣው የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች ቡድን ስኬታማ ቆይታ አድርጎ መመለሱን የገለጸ ሲሆን ያልተስማሙባቸው ጉዳዮች እንዳሉ እና ተጨማሪ ውይይቶች በቀጣይ እንደሚደረጉም አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ11 ዓመት በፊት በዩሮ ቦንድ የገዛችውን አንድ ቢሊዮን ዩሮ መክፈል ባለመጀመሯ ምክንያት ከጋና እና ዛምቢያ በመቀጠል ሶስተኛ ሀገር መባሏ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የዩሮ ቦንድ ብድሩን መክፈል ያልጀመርነው በገንዘብ እጥረት ሳይሆን ሁሉንም አበዳሪዎቻችንን እኩል ማየት አለብን ብለን ስለምናምን ነው ስትል ምላሽ መስጠቷ አይዘነጋም፡፡
ኢትዮጵያ 29 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ብድር ያለባት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሹ ከቻይና የተገኘ ሲሆን የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላት በመጠየቅ ለይ ትገኛለች፡፡
የብድር ጫና ካለባቸው ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ከቻይና ውጪ ያሉ ሀገራ እና አበዳሪ ተቋማት የብድር መክፈያ ጊዜን እስካሁን ለማራዘም ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ ከታማኝ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት 10 ቢሊዮን ዶላር ብድር ከፍላለች ብለዋል፡፡