ኢትዮጵያ ከአራት ቀናት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት በምስራቅ አፍሪካ አዲስ ትኩሳት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነ ሲሆን ሀገራት በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
ሱማሊላንድ አንድ አካሌ ናት የምትለው ሶማሊያ ስምምነቱን እንደ ወረራ እንደምትመለከተው ገልጻ ተመድ፣ አፍሪካ ህብረት ፣ የአረብ ሊግ እና ሀገራት ከጎኗ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርባለች፡፡
አሜሪካ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ የሰጠች ሲሆን ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና መስጠት ስህተት እንደሆነ ገልጻለች።
የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር እንዳሉት “የሶማሊያን ሉዓላዊነት ከማክበር ባለፈ እውቅና ትሰጣለች፣ በአፍሪካ ቀንድ የተፈጠረው አዲስ ውዝግብም ያሳስበናል” ብለዋል።
“ሁሉም አካላት ጉዳዩን ከማካረር ሊቆጠቡ ይገባል” ያሉት ቃል አቀባዩ “አለመግባባቱን በዲፕሎማሲያዊ ድርድር ሊፈቱ ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ክልል (ሶማሊላንድ) መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም የተፈጠረውን ውጥረት በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለማርገብ መረጋጋት እና መከባበር እንዲኖር ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በመካከላቸው ያለው መልካም ግንኙነት ሊያበላሽ ከሚችል ማንኛውም ተግባር እንዲታቀቡም ህብረቱ በመግለጫው አሳስቧል።
ሊቀመንበሩ አክለውም የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ መንግስታትን ጨምሮ ሁሉንም የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት አንድነትን፣ የግዛት አንድነትን እና ሙሉ ሉዓላዊነትን ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል ።
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዘላቂ ሰላምን፣ ደህንነትን እና መረጋጋትን ለማስፈን እና ለማጠናከር የመልካም ጉርብትና ደንቦችን ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ለአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔዎች መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአረብ ሊግ በበኩሉ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ያደረጉትን ስምምነት እንደማይቀበል አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ “የሶማሊያን ሉዓላዊነት እንደሚያከብር፣ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገው ስምምነትም ይህንን የማይጥስ ነው” ማለቱ ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ በጉዳዩ ዙሪያ በወጣው መግለጫ ህብረቱ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እንደሚያከብር ገልጿል፡፡
የሶማሊያ ሉዓላዊነት መከበር አለበት ያለው የአውሮፓ ህብረት የሀገር አንድነትን ለማክበር የሶማሊያን ህገ መንግስት፣ የአፍሪካ ህብረት እና ተመድ ህግጋቶችን ማክበር ያስፈልጋልም ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ እስከ 20 ኪሎ ሜትር የሚዘልቅ ወደብ እና ወታደራዊ ማዘዣ መገንባት የሚስችላት ሲሆን ለሶማሊላንድ ደግሞ የሀገርነት እውቅና እንዲሰጥ ይደነግጋል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ልገለል አይገባም፣ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትም የበህር በር ያስፈልገኛል ማለቷ ይታወሳል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የደህንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ዛሬ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መግባቢያ ስምምነት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የደህንነት አማካሪው በዚህ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ወደብ ለማግኘት ከኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ መሪዎች ጋር ውይይት ማድረጓን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ሶስቱም የቀይ ባህር ሀገራት ለኢትዮጵያ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው አውቀናል ያሉት ሬድዋን ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት ለመፈራረም ተገደናል ሲሉ ለዲፕሎማቶቹ አብራርተዋል፡፡