አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሕዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም በሚካሄደው የቫሌንሺያ ማራቶን እንደሚሳተፍ አስታውቋል፡፡
አትሌቱ በፌስቡክ ገጹ እንዳለው “ከብዙ ጊዜ ጉዳት በኋላ በቫሌንሺያ ማራቶን እሳተፋለሁ” ብሏል።
“ከብዙ ጉዳት በኋላ ወደ ውድድር በመመለሴ ደስተኛ ነኝ” ያለው አትሌት ቀነኒሳ አኤኤንቲኤ የተሰኘው ኩባንያ ስፖንሰሬ ነው፣ ላደረገልኝ ድጋፍ አመሰግናለሁ ” ሲልም ገልጿል።
ውድድሩ የፊታችን ሕዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም በስፔኗ ቫሌንሲያ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
አትሌት ቀነኒሳ በአምስት እና አስር ሺህ ውድድሮች ላይ ለዓመታት ሳይረታ የቆየ ውጤታማ አትሌት ሆኖ ቆይቷል።
በሁለቱም ርቀቶች የዓለም ሪከርዶችን ለ16 ዓመታት ይዞ የቆየው አትሌት ቀነኒሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፊቱን ወደ ማራቶን ውድድር አዙሯል።
የማራቶን ውድድርን ከሁለት ሰዓት በታች ይገባል ተብሎ ከሚጠበቁት የዓለም ማራቶን ሯጮች መካከል ዋነኛው ነውም ተብሏል።
አትሌት ቀነኒሳ በዓለም የሀገር አቋራጭ ውድድሮች የምንጊዜውም ስኬታማ አትሌት ሲሆን 11 ጊዜ የሀገር አቋራጭ ውድድሮችን በአንደኝነት አጠናቋል።
በጀርመን አዘጋጅነት በ2009 በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር በአምስት ሺህ እና 10 ሺህ ውድድሮችን በአንደኝነት ማጠናቀቅም ችሏል።
በ2014 በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው የማራቶን ውድድር ያስመዘገበው ውጤት ስድስተኛው የምንግዜውም ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።
ከሁለት ዓመት በኋላም በ2019 በርሊን ማራቶንን በ2:01:41 ሰዓት በአንደኝነት ያጠናቀቀ ሲሆን ከቀናት በኋላ በቫሌንሲያ በሚካሄደው የማራቶን ውድድር ላይ ለውጤት ይጠበቃል።