የኤሌክትሪክ ኃይል በተያዘው ዓመት ከሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገራት ከተሸጠ የኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ 30 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ሁለት ሺህ ከ993 በላይ ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ይደረጋል፡፡
ለሦስት ጎረቤት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማለትም ለሱዳን፤ ኬንያ እና ጅቡቲ 2 ሺህ 993 ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት በማድረግ 182 ሚሊዮን ዶላር ወይም 10 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል፡፡
ለሀገር ውስጥ ደንበኞች በሚሸጥ የኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ 20 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱንም አቶ ሞገስ ተናግረዋል፡፡
ባሳለፍነው የ2015 በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ እና ለጎረቤት ሀገራት በተሸጠ ኤሌክትረክ ሀይል 22 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት ለመሸጥ አቅዳ እየሰራች ነው የተባለ ሲሆን ከታንዛኒያ ጋር ድርድሮች በመካሄድ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ ስምምነት በተያዘለት ጊዜ ከተጠናቀቀ በዚህ ዓመት ሀይል ዳሬሰላም መላክ እንደሚጀመር ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከታንዛኒያ በተጨማሪም ለደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ የኤሌክትሪክ ሀይል ለመሸጥ እቅድ መያዙ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል መግለጹ ይታወሳል፡፡
የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት የሚያገኙ ኢትዮጵያዊያ 52 በመቶዎቹ ብቻ ሲሆኑ የሀገር ውስጥ ፈላጎት ሳይሟላ ሀይል ለምን ወደ ጎረቤት ሀገራት ይላካል የሚሉ ወቀሳዎች በመንግስት ላይ እየተሰሙ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በበኩሉ ሀይል ወደ ጎረቤት ሀገራት የምልከው ስራዎች በሚቆሙባቸው ሰዓታት በተለይም ሌሊት ላይ ነው ያለ ሲሆን ሽያጩ መንግስት የገጠመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት ሲባልም ነው ብሏል፡፡