የገንዘብ ሚኒስቴርና የዓለም ባንክ ለአፍሪካ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ፕሮጀክት (በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር ፕሮጀክት) የ730 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት መፈራረማቸው ይፋ ተደርጓል።
ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን 90 በመቶ የባህር ንግድን የሚይዘው ስትራቴጂካዊው ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ ኮሪደር ጋር በተሳሰረ መልኩ የኢትዮጵያን የሎጅስቲክስና የትስስር አቅም እንደሚያጎለብት ተጠቁሟል።
በስምምነቱ መሰረት ለሜኦሶ-ድሬዳዋ መንገድ ግንባታ የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን፤ ግንባታው የትራንስፖርት አቅምና ብቃት የሚጨምር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
መንገዱ በሚገነባባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች የጤና፣ ውሃና ትምህርት አገልግሎት ተደራሽነት ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ድጋፍ እንደሚደረግም ተመላክቷል።
ፕሮጀክቱ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሺዬቲቭ አካልና የቀጣናዊ ትብብር ማዕቀፍ እንደሆነ ያመለከተው ሚኒስቴሩ፤ ማዕቀፉ አካባቢውን በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ፋይዳም እንዳለው ተጠቅሷል።
ስምምነቱን የተፈራረሙትም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና የዓለም ባንክ የቀጣናዊ ትስስስር ዳይሬክተር ቡቴይና ጉርማዚ ናቸው።
አቶ አህመድ ሺዴ ለዓለም ባንክ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ኢትዮጵያ “ለቀጣናዊ ትስስር መጎልበት በቁርጠኝነት ትሰራለች” ብለዋል።
የመሰረተ ልማት እድገት ለቀጣናው የረጅም ጊዜ ልማትና መረጋጋት ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለውም መገለጹን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።