የብሪክስ መሪዎች ዓመታዊ ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ መካሄድ ጀመረ

ከ15 ዓመት በፊት በብራዚል፣ ሩሲያ፣ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የተመሰረተው ብሪክስ የዘንድሮውን ጉባኤ በጆሀንስበርግ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ፣ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ተገኝተዋል፡፡

ሩሲያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጊ ላቭሮቭ የተወከለች ሲሆን ፕሬዝዳንት ፑቲን በበይነ መረብ ታግዘው ንግግር አድርገዋል፡፡

የጉባአው አዘጋጅ ደቡብ አፍሪካ ለ60 ሀገራት ግብዣ ያቀረቡ ሲሆን ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በጉባኤው ላይ እንዲገኙ መጋበዛቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ የዓለማችን ሀገራት የብሪክስ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ አምሬት፣ ግብጽ፣ አልጀሪያ እና ሌሎችም ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ያቀረቡ ሀገራት ናቸው፡፡

የብሪክስ መስራች ሀገራት አሁን ላለው የዓለም ስርዓት ተጻራሪ የሆነ የግብይት እና የትብብር መንገድ መፍጠር ዋነኛ አላማቸው እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ብሪክስ የቡድን ሰባት ሀገራት ስብስብን የሚገዳደር እንዲሆን ይፈልጋሉ የተባለ ሲሆን በምዕራባዊያን የበላይነት የተያዘው የዓለም ስርዓት መቀየር አለበትም ብለው ያምናሉ ተብሏል፡፡

የብሪክስ ሀገራት በዶላር የበላይነት ላይ የተመሰረተውን ዓለም ንግድ እና ኢንቨስትመንት ለመቀየር የራሳቸውን መገበያያ እና ባንክ በማቋቋም ላይ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡

አሜሪካ ብሪክስን በጂኦ ፖለቲካ ተገዳዳሪ ሀይልነት እንደማታየው ከሰሞኑ መግለጿ ይታወሳል፡፡

በጆሀንስበርግ ለሶስት ቀናት እየተካሄደ ያለው የብሪክስ ጉባኤ አባል ለመሆን ላቀረቡ ሀገራት ጥያቄ ዙሪያ ይመክራል የተባለ ሲሆን ቢያንስ አምስት ሀገራትን በአባልነት እንደሚቀበል ይጠበቃል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *