ዳሸን ባንክ እና ማስተር ካርድ በጋራ በመተባበር “ቨርቹዋል የቅድመ ክፍያ ካርድ” የተሰኘ አገልግሎት በይፉ አስተዋውቀዋል፡፡
ካርዱ ከተለደው እና በሥም ከሚታተመው የፕላስቲክ ካርድ የተለየ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ደንበኞች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሆነው ገንዘባቸውን መጠቀምና ማንቀሳቀስ የሚችሉበት አማራጭ ነው ተብሏል።
የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ እንዳሉት “ዳሸን ባንክ ይህን በአይነቱ የተለየ ካርድ ማስተዋወቁ፤ ባንኩ ለደንበኞቹ ቀላል፣ ምቹና አስተማማኝ የፋይናስ አገልግሎቶችን ይበልጥ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል” ብለዋል፡፡
ዳሽን ባንክ ከዚህ ቀደም “የውጪ ምንዛሬ ሂሳብ” ላላቸው ደንበኞቹ ብቻ የሚያገለግል ካርድ በሥራ ላይ ማዋሉን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ አዲስ የተዋወቀው “ቨርቹዋል የቅድመ ክፍያ ካርድ” በአጠቃላይ ለአለም ዓቀፍ ተጓዦች ታስቦና ከፍተኛ የደህንነት መጠበቂያ ተደርጎለት በአማራጭነት የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።
ደንበኞች ካርዱን ለመጠቀም አቅራቢያቸው በሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ ፓስፖርት፣ ቪዛ እና የበረራ ቲኬት በመያዝ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉም ብለዋል፡፡
ቨርቹዋል የቅድመ ክፍያ ካርዱ ከሌሎች የቅድመ ክፍያ ካርዶች የተለየ አማራጮችን ይዞ መምጣቱም ተገልጿል።
ካርዱ ከተሰጠ በሗላ ደንበኞች ለራሳቸው በተዘጋጀ ፓርታል ላይ ገብተው በካርዱ ላይ ያለውን የሚስጥር ቁጥር መቀየር፣ ካርዱ ቢሰረቅ የካርዱን እንቅስቃሴ ማስቆም እንዲሁም የተከናወኑ ግብይቶችን ማረጋገጥ እንደሚያስችልም አቶ አስፋው ተናግረዋል።