በኢትዮጵያ የተቀበሩ ፈንጂዎች ፈንድተው 23 ህጻናት መገደላቸው ተገለጸ

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የነበረው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈረመ ስምምነት መሰረት ማብቃቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንዳለው ሲቪል ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ፣ በእርሻ ፣ በውሃ መቅጃ እና በገበያ ቦታዎች እንዲሁም የትምህርት ወይም የጤና ተቋማትን የመሳሰሉ የዕለት ተዕለት መሠረታዊ ሕይወት ወደሚከወኑባቸው ሥፍራዎች በሚወስዱ መንገዶች አካባቢ የተቀበሩ ፈንጂዎች ፣ የተጣሉ ቦምቦች ፣ የከባድ መሣሪያ ቅሪቶች እና በቀላል ንክኪ የሚፈነዱ ሌሎች መሣሪያዎች በሰዎች ሕይወት ፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛል ብላል።

ኮሚሽኑ ይህን በተመለከተ ባደረገው ክትትል በአፋር ክልል ፣ ካሳጊታ ከተማ በአንድ መኖሪያ አካባቢ በድንገት በፈነዳው የሞርታር ጥይት ምክንያት 4 ሰዎች ወዲያው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን በከፍተኛ ደረጃ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 5 ሰዎች ወደ ዱብቲ ሆስፒታል ተወስደዋል ብሏል፡፡

ግለሰቦቹ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላም አንድ ሕፃን ሕይወቱ ማለፉን ኮሚሽኑ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከአፋር ክልል አድዓር ወረዳ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት በተገኘ መረጃ መሠረት 23 ሕፃናት በፈንጂ ጉዳት እንደሞቱ ፣ እንዲሁም ወደ 20 የሚገመቱ ተጨማሪ ሕፃናት ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ለመረዳት መቻሉን አሳዉቋል፡፡

የአፋር ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሀላፊ አቶ መሀመድ አሊን እንዳሉት ከጦርነቱ በኋላ በተቀበሩ እና በተተዉ ፈንጂዎች የሰዎች ህይወት እያለፈ መሆኑን ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት ከጦርነቱ በኋላ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ቅሪቶችን ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር የማጽዳት ስራ ማከናወኑን አሁንም እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ የመረጃ ልዉዉጥ እና ሰዎች ወድቀዉ የሚያገኟቸዉን ብረታብረቶች መነካካት እንዲሁም ማንሳትና ወደ መኖሪያቸዉ መዉሰድ እንደሌለባቸዉ የማስተማር ስራ እየሰሩ መሆኑን አክለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት አንድ ሚሊዮን ገደማ ዜጎች እንደተገደሉ ሲገለጽ ከ20 ቢሊዮን በላይ ዶላር ጉዳት ማድረሱን የገንዘብ ሚንስቴር መግለጹ ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *