ቤተ ክርስቲያኗ በትግራይ ክልል ያሉ የአራት ሊቀ ጳጳስን ክህነት አነሳች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትግራይ ክልል የተሰጠው ኤጲስ ቆጵሳት ሹመት ህገወጥ መሆኑን አስታውቃለች።

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተፈጠረው ወቅታዊ የዶግማ፣ የቀኖናና የአስተዳደራዊ ጥሰቶችን አስመልክቶ ውሳኔዎች አሳልፌያለሁ ብሏል።

ቤተ ክርስቲያኗ አክላም ከፍተኛውን ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲወጡ አደራ በተሰጣቸው ሊቃነ ጳጳሳት በማኅበረሰብ ዕድገትና አስተዳደር ውስጥ ከሕዝብ ጋር በቆመች፣ ከፖለቲካ በጸዳች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ መንፈሳዊና ሕዝባዊት ተቋምነቷን በመካድ ከፍተኛ የሆነ ሕገ ወጥ ድርጊትና ተቋምን የመናድ እንደሁም መዋቅሯን የማፍረስ ተግባር ተከናውኖብኛል ብላለች።

ሐምሌ 16 እና 23 ቀን 2015 ዓ/ም በክልል ትግራይ በማእከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ገዳም ውስጥ የተፈጸመውን ሕገወጥ የሆነ አስነዋሪ፤ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት መፈጸሙንም ቤተ ክርስቲይኗ በመግለጫው ላይ ጠቅሳለች።

ሐምሌ 16 እና 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በክልል ትግራይ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ገዳም ውስጥ በትግራይ ክልል በሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት፡-

አባ ኢሳይያስ፣ አባ መቃርዮስ ፣አባ መርሐ ክርስቶስ እና አባ ጴጥሮስ መሪነት አሳዛኝ ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ አስነዋሪ፣ ሕገ-ወጥ፣ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት መፈጸማቸው ተገልጿል።

አራቱ የሀይማኖት አባቶችም 10 መነኮሳትን በእጩነት በመምረጥና ለዘጠኙ ህገወጥ ሲመት በመፈጸም፣ ሥርወ ትውፊት ዘሐዋርያት የሆነውን የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ መንበር በመካድ “መንበረ ሰላማ” የሚባል ህገወጥ መንበር ሰይመዋልም ተብሏል።

እንዲሁም በህገወጥ መንገድ የሾሟቸውን ግለሰቦች ሊቃነ ጳጳሳት በሚመሯቸው በሀገር ውስጥና በውጪ በሚገኙ አህጉረ ስብከት በሕገ ወጥ መንገድ በመመደብ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አልፎ አንዲት ኩላዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የሚከፋፍል፤ የሀገር አንድነትን የሚሸረሽር እና የሚያፈርስ፣ ምእመናንን ከምእመናን፣ ካህናትን ከካህናት፣ ሊቃውንትን ከሊቃውንት ወጣትን ከወጣት የሚያጋጭ ሰላም የሚያናጋ ተግባር መፈጸማቸው ተገልጿል።

ይህን ህገወጥ ተግባር ለመፈጸም በሀገራችን ተከስቶ የነበረው ጦርነት እንደ ምክንያት የተጠቀሰ ቢሆንም ቤተክርስቲያን ከጦርነቱ በፊት ጦርነት እንዳይከሰት ያደረገችውን ጥረት በጦርነቱ ወቅት ለተደረጉ ድጋፎችና ከጦርነቱ በኋላ ለተደረጉ የእንወያይ ጥረቶች እንዲሁም በቤተክርስቲያን በኩል የተዘረጋውን የሰላምና የእርቅ በር ይልቁንም ለሰላም ሲባል በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የተጠየቀውን ይፋዊ ይቅርታ በመግፋት የተደረገ ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር ነውም ተብሏል።

በዚህም መሰረት በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 16 ንዑስ ቁጥር 30 የአጲስ ቀጶሳት መሾም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት እንዲመረጡና እንዲሾሙ የመወሰን ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ መሆን የሚደነግገውን ክፍል በግልጽ መጣሱ ተገልጿል።

በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 31 ንዑስ ቁ 1 እና 3 የቅዱስ ፓትርያርኩን የመዓርግ ስምና መንበር በተመለከተ የተደነገገውን ድንጋጌ የሚያፋልስ ህገወጥ ተግባር የተፈጸመ ነውም ተብሏል።

በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 37 ንዑስ ቁ.1 የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሚፈጸመው ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስፈላጊ መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲታመንበትና ሲወሰን ብቻ እንደሚፈጸምና ተደንግጎ ሳለ ድርጊቱ ህገወጥ እንደሆነ ቤተ ክርስቲያኗ አስታውቃለች።

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 138 መሠረት ሐምሌ 16 እና ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በክልል ትግራይ በማዕከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ውስጥ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ የመቀሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የእንቅስቃሴው ሰብሳቢ፣ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በክልል ትግራይ የማዕከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የአዲግራት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ባልተሰጣቸው ስልጣን 9 ኤጴስ ቆጰሳትን ሾመናል፤ ሲኖዶስ አቋቁመናል በማለታቸው
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የሚኖረውን ሕዝበ ክርስቲያንን በማታለል የክህደት እና የኑፋቄ ተግባር በመፈጸማቸው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ፤ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት መሻሩ ተገልጿል።

በተጨማሪም ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ የተነሣ ስለሆነ ከዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ፤ በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ተለይተዋል ተብሏል፡፡

ከላይ በስም ተጠቅሰው የተወገዙት ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም የቅዱስ ሲኖዶሱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልና በመዳፈር እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በተነሳሱ ግለሰቦች አማካኝነት የኤጲስ ቆጶስነት ሹመት አግኝተናል፤ ተሹመናል እያሉ የሚገኙ 9 መነኮሳት ማለትም አባ ዘሥላሴ ማርቆስ ፣አባ ኃይለ ሚካኤል አረጋይ ፣አባ እስጢፋኖስ ገብረ ጊዮርጊስ ፣ አባ መሓሪ ሀብቶ ፣አባ ኤልያስ ታደሰ ገብረ ኪዳን፣ አባ ጽጌ ገነት ኪዳነ ወልድ ፣አባ ዘርአ ዳዊት ብርሃነ ፣አባ ዮሐንስ ከበደ እና አባ የማነ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል በሕገ ወጥ መንገድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንን ጥሰው የተገኙ በመሆኑ አስቀድሞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት ተሽሮ ከዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያ በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ተለይተዋልም ተብሏል።

ይህ ህገወጥ ሢመት እንዲፈጸም ከመጀመሪያው ጽንሰ ሀሳብ ጀምሮ መሪ ተዋናይና ቀስቃሽ በመሆን ኢትዮጵያን ኤልዛቤል በማለትና ስሟን የሚጠራ የተረገመ ይሁን በማለት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር የዶግማ ልዩነት አለን በማለት የኑፋቄ ትምህርት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተናገሩትና በህገወጥ ሢመቱ ላይም በእጩነት ተመርጠው በሂደት ላይ ያሉት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤልና ሂደቱን በዋና አስፈጻሚነት በመምራትና መግለጫ በመስጠት ላይ ያሉት መ/ር ተስፋዬ ሐደራ ከዛሬ ሐምሌ 26 ቀን2015 ዓ/ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወግዘው ከቤተክርስቲያን መለየታቸው ተገልጿል።

በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያኗ “መንበረ ሰላማ” የሚለው ሕገወጥ ሥያሜን በተመለከተ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ትውፊትም ሆነ በቀደምት አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት የማይታወቅ፣ ሃይማኖታዊ መሠረት የሌለው፣ ከቀኖና የወጣ፣ አስተዳደራዊ መዋቅርን የሚያዛባ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደማትቀበለው አስታውቃለች።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *