በጋምቤላ በተከሰተ የብሔር ግጭት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

በጋምቤላ ክልል በአኙዋክ እና ኑዌር ብሔረሰቦች መካከል በተፈጠረዉ ግጭት እስካሁን ቁጥራቸዉ ከ30 በላይ የሆኑ ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ ተናግረዋል።

አቶ ኡገቱ ፤ ግጭቱ ግንቦት 13 ላይ አኙዋ እና ሊየር በሰተኙ በሁለት መንደሮች መካከል የተነሳ መሆኑን ገልጸዋል ።

ግጭቱ በኋላም ወደ ብሔር ግጭት እየሰፋ የመጣ መሆኑን የተናገሩት ሀላፊው ግጭቱ በተከሰተበት ወቅትም የክልሉ መንግስት ኮማንድ ፖስት በማቋቋም ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር ሁኔታዉን ለማረጋጋት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሟቾች ቁጥር 30 ደርሷል ቢባልም በጸጥታ ግብረ ሀይሉ የተረጋገጠ አይደለም ብለዋል።

ሆኖም በግጭቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችል ግን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

በግጭቱ በኢታንግ ልዩ ወረዳ 4 ቀበሌዎች ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ተፈናቅለዋል ተብሏል።

ብርሃነሰላም ፣ አዲማ ፣ አላ እና አጂዉ በተሰኙት አራት ቀበሌዎች የሚኖሩ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ተፈናቅለዉ በየቤተሰባቸው ቤት ተጠልለዉ ይገኛሉ ብለዋል።

በተመሳሳይ ኩራ ቀበሌ በከፊል ነዋሪዎች የተፈናቀሉበት መሆኑን እና በጋምቤላ ከተማም የኑዌር ብሔረሰቦች መንደር የግጭቱ ቀጠና መሆናቸዉን አክለዋል።

በዚህም የተፈናቃዮችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ የማጣራት ማከናወን የግድ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ ግጭቱን በማረጋጋት ሰላም ለማምጣት የሰላም ዉይይት እያደረገ ቢሆንም እስከ ቅዳሜ ድረስ ግን ግጭቱ በክልሉ ቀጥሎ ነበር።

እንደ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊዉ ገለጻ ግጭቱን የሚፈልጉ አካላት አሉ ያሉ ሲሆን ፤ አለመረጋጋቱ ግን ከመንግስት አቅም በላይ አይደለም ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ በጋምቤላ ክልል እየተፈጠረ ያለው የጸጥታ ችግር ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን ገልጾ የፌደራል መንግሥት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ አሳስቧል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *