እናት ባንክ “ለእናቴ” የተሰኘ አገር አቀፍ ጽሑፍ ውድድር  ጀመረ



እናት ባንክ “ለእናቴ” የተሰኘ ኹሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የሚያሳትፍና የሚያሽልም አገራዊ የጽሑፍ ውድድር መጀመሩን አስታውቋል።

የባንኩ ማርኬቲንግ እና ኮሙንኬሽን ዳይሬክተር አቶ አክሊል ግርማ እንዳሉት “ውድድሩ እናት ባንክ ከተመሠረተበት ራዕይና ተልዕኮ አንፃር የሚዛመድ ብሎም የባንኩን ማኅበራዊ እሴት ማዕከል የሚያደርግ አገር አቀፍ መርሐ ግብር ነው” ብለዋል።

አቶ አክሊል አክለውም ባንኩ ለዘመናት ለአገርም ሆነ ለቤተሰብ ምሰሶ ለሆኑት የኢትዮጵያ እናቶች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ለአንድ ወር የሚቆይ ሽልማት የሚያስገኝ፣ “ለእናቴ” የተሰኘ የጽሑፍ ውድድር በይፋ ማስጀመሩን ተናግረዋል።

ውድድሩ በዋናነት ኹሉም ሰው ለእናቱ ያለውን ፍቅር፣ አክብሮት፣ ውለታና ምስጋና በዝርዝር ጽሑፍ ማለትም ግጥም ባልሆነ በወግ መልክ ወይንም በደብዳቤ ቅርፅ የሚገልጽበትና “ለእናት” የሚልበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ጨምረው አስረድተዋል።

“ኹሉም ሰው ለእናቱ ያለውን ፍቅርና ስሜት የሚገልጽበት የራሱ ስሜት አለው።” ያሉት ደራሲና ጋዜጠኛ ቴድሮስ ተክለአረጋይ፤ ይህም ውድድር ሰዎች ለእናታቸው ያላቸውን ስሜት በጽሁፍ የሚያወጡበትና በዚህም ጽሁፍ ተወዳድረው በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና እና ሽልማት ያገኙበታል ብለዋል።

አጠቃላይ የውድድሩ ይዘት ተወዳዳሪዎች “ለእናቴ” ብለው ስለእናታቸው የሚያጋሩትን ፍቅርና ስሜት ዳኞች አወዳድረው የሚያበላልጡበት ሳይሆን፤ ይልቁንም ተወዳዳሪዎች ለእናታቸው ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት እንዴት እንደገለጹ፣ ስሜታቸውን ወደሌሎች ለማጋባት እንዴት እንደጣሩ የሚዳኙበት ዐውድ መሆኑንም ደራሲ ቴድሮስ አክለዋል።

የጽሁፍ ማወዳደሪያው መስፈርትና የውድድሩ ዳኝነት፤ በቋንቋና በጽሑፍ ተግባቦት ሰፊ ልምድ ባላቸው ከፍተኛ ባለሙያዎች እንደተዘጋጀ ሁነቱን አስመልክቶ በተዘጋጀ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

የማወዳደሪያ መስፈርቶቹም በተመሳሳይ መልኩ የተቃኙ ሲሆኑ፤ የቅርፅ ጉዳዮች 50 ከመቶ፣ የይዘት ጉዳዮች 50 ከመቶ፣ በድምሩ 100 ነጥብ እንዲይዙ ተደርገው ተዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡

ለውድድሩ የሚያቀርቡት ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ በሆነው አማርኛ ቋንቋ መቅረብ አለባቸው የተባለ ሲሆን፤ በሌሎች የኅትመት እና የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ያልቀረበ ወጥ፣ አዲስና የተለየ መሆን አለበትም ተብሏል።

በዚህም መሠረት ጽሑፉ፤ ግልጽ እና ተነባቢ እንዲሆን በኮምፒውተር ተጽፎ፣ በ12 “ፎንት” የፊደላት መጠን እና በ1.5 የኅዳግ መስመር መቅረብ እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን፤ በ ኤ ፎር (A4) የወረቀት ምጣኔ፣ ከሦስት /3/ ገጽ ያልበለጠ መሆን ይኖርበታል ተብሏል።

በተጨማሪም ተወዳዳሪዎች ሥማቸውን እና አድራሻቸውን የጽሐፍ ሥራቸውን ባቀረቡበት ወረቀት ላይ ሳይሆን፤ ሥራቸውን በሚያሽጉበት ፖስታ ላይ ብቻ መጻፍ ይጠበቅባቸዋል የተባለ ሲሆን፤ እናት ባንክ፥ አሸናፊ ጽሐፎችን በተለያዩ መንገዶች ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ተገልጿል።

በተለየ ሁኔታ ጽሁፋቸውን በወረቀት ማቅረብ ያልቻሉ ከአገር ውጪ የሚገኙ ተወዳዳሪዎችም ጽሁፋቸውን በ Lenat@enatbanksc.com ላይ ማቅረብ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ተወዳዳሪዎች የጽሁፍ ሥራቸውን ከሚያዚያ 26 ቀን 2015 ጀምሮ እስከ ግንቦት 23 ቀን 2015 ባሉት የሥራ ቀናት በአቅራቢያቸው ሚገኙ የእናት ባንክ ቅርንጫፎች በአካል በመገኘት ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *