የኢትዮጵያ ሚዲያዎች በጥቃት ውስጥ እንደሚገኙ ተገለጸ

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ 29 ጋዜጠኞች በታሰሩባት ኢትዮጵያ፤ የፕሬስ ነጻነት “ጉልህ ጥቃት” እንዳጋጠመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የደቡባዊ አፍሪካ ሚዲያ ኢንስቲትዩት አስታወቁ።

ባለስልጣናት የፕሬስ ነጻነትን ማፈን በሚፈልጉባቸው በምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት፤ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየጨመረ መምጣቱንም ተቋማቱ ገልጸዋል።

ሁለቱ ተቋማት ይህን ያሉት ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 25፤ 2015 ታስቦ የሚውለውን የዓለም የፕሬስ ነጻነትን በማስመልከት በጋራ ባወጡት ዳሰሳ ነው።

ዳሰሳው ኢትዮጵያን ጨምሮ በ10 የአፍሪካ ሀገራት ያለውን የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን እና በጋዜጠኞች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን በማሳያነት በማንሳት ዳሰሳ አድርጓል።

በዚሁ ዳሰሳ፤ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ከኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በመለጠቅ ስሟ የተጠቀሰው ኢትዮጵያ ነች።

እንደ ሁለቱ ተቋማት ዳሰሳ ከሆነ በ2022 ብቻ በኢትዮጵያ 29 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች ታስረዋል።

ከእነዚህ ጋዜጠኞች አምስቱ “ከጠላት ጋር ተባብራችኋል” በሚል በትግራይ ባለስልጣናት የታሰሩ እንደነበሩ ዳሰሳው አመልክቷል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ታስሮ የነበረው የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂነግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ ጉዳይም በአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የደቡባዊ አፍሪካ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ዳሰሳ ላይ ተነስቷል።

“ወታደራዊ ምስጢሮችን ለማይመለከተው አካል በግልጽ በመጻፍ” እና “ሐሰተኛ ጽሁፎችን” በማሰራጨት ተከስሶ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ባለፈው ህዳር ወር በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቱን ዳሰሳው አስታውሷል

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *