አዲስ በተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ እና ጀነራል ፃድቃን ገብረተንሳይ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ተደርገው ተሾመዋል።
ይኸው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር 27 አባላት ያሉትን ካቢኔ ይፋ ባደረገበት ወቅት ተገልጿል።
በአዲሱ ካቢኔ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የሰላም እና ጸጥታ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፣ ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ደግሞ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነዋል።
ሹመቱ በመቐለ ከተማ ይፋ ሲደረግ የክልሉን መንግስት ሲመራ የነበረው የቀድሞ ካቢኔ፤ የአስፈጻሚነት ስልጣኑን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ለተቋቋመው አዲሱ ካቢኔ አስረክቧል።
አዲሱ ካቢኔ የተዋቀረው ከህወሓት፣ ከትግራይ ኃይሎች፣ ከምሁራን እና ከብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) ፖለቲካ ፓርቲ የተውጣጡ አባላትን በማካተተት ነው። የካቢኔው 51 በመቶ ቦታ የተያዘው በህወሓት ሲሆን፤ ተቃዋሚው ባይቶና ፓርቲ ሁለት ቢሮዎችን በኃላፊነት የመምራት ዕድል አግኝቷል።
ከትግራይ ኃይሎች በካቢኔው ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ያገኙት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ፣ ብርጋዴር ጄነራል ተኽላይ አሸብር፣ ሌተናን ጄነራል ፍሰሃ ኪዳኑ እና ሜጀር ጄነራል ዘውዱ ኪሮስ ናቸው።