የኦሮሚያ ክልል ያለበቂ ማጣራት ህጋዊ ቤቶችን እያፈረሰ እንደሆነ ኢሰመኮ ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቅርቡ በአዲስ መልክ በተደራጀው የሸገር ከተማ አስተዳደር የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት እየተከናወነባቸው ባሉ አካባቢዎች ምርመራ ማካሄዱን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ምርመራ ካደረገባቸው አካባቢዎች መካከል ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ መነ አብቹ እና በዙሪያው የሚገኙ አካባቢዎች ዋነኞቹ ናቸው።

ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች በግል እና በቡድን ለኮሚሽኑ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ከየካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል።

ለኮሚሽኑ ቅሬታ ያቀረቡ ሰዎችን፣ የሚመለከታቸውን የከተማ አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት በማነጋገር፤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳት ሂደቱ የሚከናወንበትን ሁኔታ እንዲሁም ቀደም ሲል የፈረሱ ቤቶችን የመስክ ምልከታ በማድረግ መረጃ እና ማስረጃ ሰብስቤያለሁም ብሏል።

ለኢሰመኮ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሰዎች ለኮሚሽኑ ሲያስረዱ በየአካባቢው ከቀድሞ/ነባር ባለ ይዞታዎች ቦታ ወይም ቤት በመግዛት ኑሮ መሥርተው ሲኖሩ የነበሩ መሆናቸውን፣ በየአካባቢው ከሚገኙ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውሃ እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩ መሆናቸውን፣ ለተለያዩ የአካባቢው የልማት ሥራዎች እንደ ማንኛውም ማኅበረሰብ ክፍያዎችን ሲከፍሉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል ተብሏል።

መኖሪያ ቤቶቻቸው ያለ በቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከሕግ አግባብ ውጭ እንደፈረሱባቸው ነዋሪዎቹ ለኮሚሽኑ ተናግረዋል።  

ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የሸገር ከተማ ኃላፊዎች በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ እንደ አዲስ መመሥረቱን ተከትሎ “ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸውን” ግንባታዎች በማፍረስ ላይ እንደሚገኝ ገልጸውልኛል ብሏል፡፡

እንዲሁም የአየር ካርታን ጨምሮ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው፣ ከነባር የአርሶ አደር ይዞታ ውጪ የሆኑ እና በተለይም ከ2005 ዓ.ም. በኋላ የተገነቡ ቤቶች እንዲፈርሱ በተወሰነው መሠረት የተከናወነ መሆኑን፣ ቤቶቹን የማፍረስ ሂደቱን በተመለከተም ከቤቶቹ ባለቤቶች ጋር በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ውይይት ተደርጎ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረጉንም ከአስተዳድሩ መስማቱን ኮሚሽኑ አክሏል።

ኢሰመኮ በጉዳዩ ዙሪያ በለገጣፎ ለገዳዲ፣ በሰበታ አካባቢ ፉሪ እና ለቡ ተክለሃይማኖት እንዲሁም በቡራዩ ገፈርሳ ኖኖ አካባቢዎች በመዘዋወር ቀደም ሲል የፈረሱ እና የማፍረስ ተግባሩ እየተከናወነ የነበረባቸውን አካባቢዎች መመልከቱን በሪፖርቱ ገልጿል።

ኮሚሽኑ በለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ በመገኘት እየፈረሱ የነበሩ ቤቶችንም የተመለከተ ሲሆን በምልከታው የቤት ማፍረሱ እና በግዳጅ ማስነሳቱ በግብረ ኃይል እየተከናወነ እንደነበረ እና በቦታው ከፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ዱላ የያዙ ሲቪል ሰዎች እንደነበሩም ተመልክቻለሁ ብላል። 

የክትትልና የምርመራ ሥራው ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም እስካሁን በተገኙት መረጃዎች እና ማስረጃዎች መሠረት የቤት ማፍረስ እና በግዳጅ የማንሳት እርምጃው ከሰብአዊ መብቶች አኳያ የታዩበትን ክፍተቶች እና ሊወሰዱ የሚገባቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች በተመለከተ ኢሰመኮ የሚከተለውን ይገልጻል፡፡ 

በዓለም አቀፍ ሕግ እና የሰብአዊ መብቶች መርሆች መሠረት በግዳጅ ማንሳት ማለት አንድን ሰው ወይም ቤተሰብ ወይም ማኅበረሰብ ከሚኖርበት ቤት ወይም ቦታ ላይ ያለ ፈቃዱ፣ አማራጭ መፍትሔ ሳይሰጠው ወይም ሕጋዊ ጥበቃ ሳይደረግለት በጊዜያዊነት ወይም በዘላቂነት በኃይል አስገድዶ ማንሳትን የሚመለከት ነው፡፡  

የቤት ፈረሳውና በግዳጅ ማንሳቱ የሚመለከተው የከተማውን መሪ ዕቅድ በሚጥሱ እና የመንግሥት ይዞታን በመውረርና ከአርሶ አደሩ ጋር በተደረገ ሕገወጥ የመሬት ግብይት የተገኙ ይዞታዎች ላይ የተደረጉ ግንባታዎችን ነው ቢባልም ሁሉም ቤቶች ግን በተመሳሳይ ሥሪት ላይ የተመሠረቱ ባለመሆናቸው የሚገዛቸውም ሕጎች እና አሠራሮች በዚያው ልክ የተለያዩ ሊሆኑ ይገባ ነበር ብሏል ኮሚሽኑ።

ኢሰመኮ ባደረገው ክትትልና ምርመራ እየፈረሱ ያሉ ቤቶች በተለያየ አይነት ክፍል የሚመደቡ መሆናቸውን አክሏል።

የመጀመሪያው ክፍል ከ2005 ዓ.ም. በፊት የተገነቡ ቤቶች ሲሆኑ እነዚህን ቤቶች በተመለከተ በሀገሪቱ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 6(4) እና (5) እንደተደነገገው አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በኢመደበኛ መልኩ የተገነቡ ቤቶች የከተሞችን ፕላን እና የሽንሻኖ ስታንዳርድ ሲያሟሉ ወደ መደበኛ ሥሪት እንደሚዞሩ ቢደነግግም ኮሚሽኑ ባደረገው ማጣራት እነዚህን ቤቶች ሕጉ በደነገገው መሠረት በወቅቱ ወደ መደበኛ ሥሪት እንዲዘዋወሩ የሚያስችላቸውን መስፈርቶች ማሟላታቸውን በማረጋገጥ የማዘዋወር ሥራ ሳይሠራ እንዲሁ እንዲፈርሱ ተደርገዋል ብላል።

ሁለተኛው ክፍል በግዢ የተገኙ ቤቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ መደበኛ ካርታ፣ የአየር ላይ ካርታ እና አረንጓዴ ደብተር ያላቸው እንዲሁም እንዳይፈርሱ የፍርድ ቤት እግድ ያለባቸው ቤቶች ከከተማ ፕላን ጋር የማይሄዱ ናቸው ከተባለ፤ በሕግ አግባብ በተደነገገው መሠረት ተለዋጭ የቤት መሥሪያ ቦታ እና ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው መነሳት የሚገባቸው ነበሩ።

ቤቶቹ በገጠር መሬት ላይ የተሠሩ ናቸው የሚባል ቢሆን እንኳ በኦሮሚያ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1999 አንቀጽ 6(8) መሠረት በቂ ጊዜ ተሰጥቶ ንብረቶቻቸውን እንዲያነሱ ይደረጋል እንጂ በድንገት ማፍረስ አይገባም እንደነበር ኮሚሽኑ አስታውቋል።  

ሦስተኛው እና አራተኛው ክፍል ከአርሶ አደሮች ጋር በተደረገ ሕገ ወጥ የመሬት ሽያጭ በተገኘ ቦታ ላይ የተሠሩ ቤቶች እና ከ2005 ዓ.ም በኋላ ያለሕጋዊ ፈቃድ በመንግሥት ይዞታዎች ላይ የተገነቡ ቤቶች ናቸው።  

ስለሆነም እንዲፈርሱ የተደረጉት ቤቶች በተለያየ አይነት ሥሪት ላይ የተመሠረቱ ስለሆነ እንደየነገሩ ሁኔታ ተገቢው መለየት እና ማጣራት እየተደረገ መፈጸም ያለባቸው ቢሆንም ሕገ ወጥ ግንባታ ማፍረስና የመንግሥት ይዞታ የሆነን ቦታ መልሶ መውሰድ ሕጋዊ እርምጃ ቢሆንም እንኳን፤ የመኖሪያ ቤት ማፍረስና በግዳጅ ማስነሳት ዜጎችን መኖሪያ ቤት አልባ በሚያደርግ መልኩ መደረግ የለበትም ብሏል ኮሚሽኑ።

እንዲሁም እንዲፈርስ የተፈለገው ቤት ያለበት የመሬት ይዞታ ዓይነት በሕግ ሊሰጥ የሚገባውን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ጊዜ መጠን የተለያየ የሚያደርገው ቢሆንም፤ ነገር ግን በማናቸውም ዓይነት ይዞታና ሁሉም ዓይነት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የመኖሪያ ቤት መፍረስ እንደሌለበት ኢሰመኮ በሪፖርቱ ገልጿል።
ይህም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሣ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1161/2011 አንቀጽ 8(8) እና የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 26(4) ላይ በግልጽ ተደንግጓል ብሏል ኮሚሽኑ፡፡  

የከተማው አስተዳደር ቤቶቹን ከማፍረሱ በፊት በቂ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን እና ከነዋሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን በዚህም ንብረቶቻቸውን በታዘዙት መሠረት ቀድመው ያነሱ ሰዎች ያሉ መሆኑን የገለጹ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ አለመደረጉን አውቄያለሁም ብላል።

ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው በርካታ ሰዎች ቤታቸው እንደሚፈርስ አስቀድሞ ያልተነገራቸው መሆኑን እና አፍራሽ ግብረ ኃይሉ በድንገት መጥቶ እንዳፈረሰባቸው ተናግረዋል።
መንግሥት የሚወስዳቸው ማናችውም እርምጃዎች ከአድሎ የጸዱ መሆን እንደሚገባቸው በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች እና በሀገር አቀፍ ሕጎች እውቅና ከተሰጠው የሰብአዊ መብቶች መርሆች መካከል አንዱ ቢሆንም ይህ ግን አልሆነም ተብላል።

ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ ባደረገባቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ አድሏዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንዳሉ ተመልክቻለሁም ብሏል።
በመሆኑም የሸገር ከተማ አስተዳድር በስመ ህገወጥ ቤቶችን ማፍረስ ስም ህጋዊ መኖሪያ ቤቶችን ከማፍረስ እንዲቆጠብ አሳስቧል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *