ቤተ-ክርስቲያኒቱ ከህግ ውጭ ሲመተ ጵጵስና የሰጡና የተቀበሉ 26 የቀድሞ አባቶችን ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ማውገዟ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሦስት ጳጳሳትንና የ20 መነኮሳትን ውግዘት አንስቷል።
ውግዘቱ የተነሳው ከዛሬ መጋቢት 21፤ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ ምልዓተ ጉባኤው አሳውቋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው “ሦስቱም የቀድሞ ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና ብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ ላይ የተላለፈው ውግዘት ከዛሬ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተነስቷል” ብሏል፡፡
በቀድሞ የሊቀ ጳጳስነት ማዕረጋቸው እንዲጠሩና ተመድበው ይሰሩበት በነበረው የስራ ኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
የየካቲት ስምንቱን ባለ10 ነጥብ ስምምነት እንቀበላለን ብለው ለቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤ ያስገቡ 20 የቀድሞ አባቶች ውግዘትም ተነስቷል።
“20ዎቹ የቀድሞ መነኮሳት አስቀድሞ በቀኖና ቤተ-ክርስቲያን መሠረት ከዲቁና እስከ ቁምስና ባለው ማዕረገ ክህነታቸው እንዲያገለግሉ እና በምንኩስና ስማቸውም እንዲጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡”
መነኮሳቱ በቀድሞው የሥራ መደብ ደረጃቸው እንዲመደቡ በመንበረ ፓትርያርክ በኩል እንዲፈጸም ትእዛዝ ተሰጥቷል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ቀሪዎቹ አምስት የቀድሞ አባቶች እንዲመለሱ በድጋሚ አሳስቧል።
ውግዘቱ ለተነሳቸው የቤተ-ክርስቲያኒቱ አባቶች በድርጊቱ የተጎዳውን መላው ህዝበ ክርስቲያን እና ቤተ ክርስቲያንን በመካስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲኖዶሱ በመግለጫው አሳስቧል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ መንግስት ቃል ገብቶ እስካሁን ያልፈታች በርካታ ሰዎች እንዲፈታልም በጥብቅ አሳስቧል።
ጥር 14፤ 2015 ዓ.ም. ሦስት ጳጳሳት በምስራቅ ሽዋ በሚገኝ ሀገረ-ስበከት 25 ኤጲስ ቆጶሳት ሾመናል ማለታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓቷና ህጓ መጣሱን ማሳወቋ አይዘነጋም።
ቤተክርስቲያኗ ጥር 18 አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምላተ ጉባኤ አድርጋም ሲመት የሰጡትን እና የተቀበሉትን ስልጣነ-ክህነታቸው እንዲነሳና እንዲወገዙ ውሳኔ አሳልፋለች።