ከስምንት ዓመት ቆይታ በኋላ አምስተኛ አልበሙን እንደሚለቅ ያሳወቀው ድምጻዊ ቴድሮስ ካሳሁን ወይም ቴዲ አፍሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ስቧል።
የፊታችን ሐሙስ ሚሚያዝያ 8፣2018 “ኢቶሪካ” የተሰኘውን የሙዚቃ አልበም ለአድማጮች እንደሚያደርስ ካሳወቀ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ዋነኛው መነጋገሪያ ሆኗል።
ድምጻዊው ስለ አዲሱ አልበሙ ሊሰጠው ያሰበው ጋዜጣዊ መግለጫ በመንግስት ተጽዕኖ ምክንያት ማካሄድ እንዳልቻለም ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም ብዙዎች ለድምጻዊው ድጋፋቸው በማሳየት ላይ ሲሆኑ ታዋቂ አርቲስቶች እና የቀድሞ ፖለቲከኞች ድጋፋቸውን ለድምጻዊ ቴድሮስ እያሳዩ ይገኛሉ።
ድምጻዊ ቬሮኒክል አዳነ በፌስቡክ ገጿ ላይ ባጋራችው ጽሁፍ “በእውቀትም፣ ዝናን በመቆጣጠርም፣ አለው አለው ባለማለትም፣ በድምፅም፣ ፍቅርን በመስበክም፣ ለህዝብ በመቆምም፣ ሀገር በመውደድም፣ ለተጎዳ በመድረስም፣ ሀይማኖትን በማክበርም፣ ለቤተሰብ ቅድምያ በመስጠትም፣ ታሪክን በማወቅም፣ እግዚአብሔርን በመፍራትም ፤ በምንም በምንም እሱን የሚያክል የለም” ብላለች።
“ቴዲ አፍሮን ሁለት ጊዜ በአካል አግኝቼዋለሁ፤ ብዙ አላወራንም ሰላምታ ብቻ ነበር” ያለችው ድምጻዊ ቬሮኒካ ቴዲ አፍሮን እንደምታደንቀው ገልጻለች።
ድምጻዊ ቬሮኒካ አክላም ቴዲ አፍሮ ከሁለት ዓመት በፊት ይህንን አዲስ አልበም የማውጣት እቅድ እንደነበረው እና ወጣት ሙዚቀኞችን ላለመጉዳት ሲል እንዳዘገየውም ተናግራለች።
ሌላኛው ወጣት ድምጻዊ ያሬድ ነጉ በበኩሉ “በተሰማራህበት የሙያ ዘርፍ ለዘመናት በመትጋት ኪነጥበብን በሚገባት ልክ አክብረሃት እሷም መልሳ ስታከብርህ አይተናል” ብሏል።
ያሬድ አክሎም “አባጣ ጎርባጣ በበዛበት የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ጎዳና በጽናት በመጓዝ ከደረስክበት ክብር መድረስህ ለምንወድህ እና ለምናከብርህ ከደስታ ባለፈ ለኛ ትልቅ መነቃቃት እና ትምህርት ሰጥቶናል። ካንተ ብዙ ተምረናል” ሲልም አክሏል።
የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙንኬሽን ሀላፊ እና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የነበሩት ዶክተር ዮናስ ዘውዴ በበኩላቸው የቴዲ አፍሮ ጋዜጣዊ መግለጫ መታገዱን ተችተዋል።
ዶክተር ዮናስ አክለውም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት “መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግለት ለቴዲ አፍሮ ደጋግሞ ጥያቄ ቢያቀርብም እምቢ ማለቱን ተናግረዋል፡፡
ቴዲ አፍሮ ከዚህ በፊት ባወጣቸው ሙዚቃዎቹ የሀገሪቱን ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ለሀገሪቱ የተለየ አብርክቶ የነበራቸውን የቀድሞ መሪዎች እና አርበኞችን ስራቸውን የሚያጎሉ ስራዎቹን ለአድማጮች አድርሷል።