በሕንፃዎችና በቤቶች ውስጥ የፀሐይ ኃይል መጠቀምን አስገዳጅ የሚያደርግ የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ያላትን የፀሐይ ኃይል በሙሉ አቅሟ ለመጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ልማትና መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ዳቢ፣ በሁሉም ሕንፃዎችና ቤቶች ውስጥ የፀሐይ ኃይል አጠቃቀምን በሒደት አስገዳጅ ለማድረግ የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን የፀሐይ ኃይል አቅም የመለየትና በምን መልኩ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚቻል የሚያሳዩ ጥናቶች መጠናቀቃቸውንም አስረድተዋል።
ከሌሎች የዓለም ሀገራት ልምድ በመውሰድ፣ በተለይም በከተሞች ረዣዥም ሕንፃዎች ባሉባቸው አካባቢዎች በእያንዳንዱ ቤትና ሕንፃ ጣሪያ ላይ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂን በመግጠም፣ ኃይል የመሰብሰብና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
ከአማራጭ ኃይል አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ያለውን አዋጭነት የሚያሳዩ ጥናቶች በስፋት እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ዘርፍ የግል ባለሀብቱ እንዲሰማራ ይበረታታል ሲሉም አክለዋል።
በሁሉም ሕንፃዎችና ቤቶች ውስጥ የፀሐይ ኃይልን መጠቀም በስፋት ሲጀመር፣ እንደ ሀገር የሚያጋጥመውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በዘላቂነት ሊያስቀር እንደሚችል አቶ መስፍን ዳቢ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የሀይል አማራጮቿን በማስፋት ልይ ስትሆን ከውሀ፣ ንፋስ፣ ከርሰ ምድር ወይም እንፋሎት እና ከጸሀይ ሀይል የተለያዩ የሀይል አማራጮችን እየተከተለች ትገኛለች።
ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ከኑክሌር ሀይል ለማመንጨት የኑክሌር ኮሚሽን ያቋቋመች ሲሆን ከሩሲያ ኑክሌር ቴክኖሎጂ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ እይዘነጋም።
የኤሌክትሪክ ሀይል ለኬንያ፣ ታንዛኒያ ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን በመሸጥ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ለሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ቡሩንዲ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ሀይል የመሸጥ እቅድም እንዳላት ተገልጿል።