ጊቭ ዋተር ከ200 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሀ ማቅረቡን ገለጸ

ሀገር በቀሉ ጊቭ ዋተር የተሰኘው ድርጅት ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት በማሰባሰብ ከ200 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንን ንጹህ የመጠጥ ውሀ ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውቋል።

የድርጅቱ ሀብት ማሰባሰብ ኃላፊ አቶ ከማል አህመድ እንዳሉት ድርጅቱ ከተመሰረተበት 2010 ጀምሮ ላለፉት 15 ዓመታት በንፁህ የመጠጥ ውሃ እጦት ክፉኛ እየተፈተኑ ላሉ የገጠር ማህበረሰብ አካባቢዎች የተለያዩ እና በርካታ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ህበረተሰቡን ተጠቃሚ መደረጉን ገልፀዋል።

ጊቭ ዎተር በ15 ዓመታት የልማት ጉዞው የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች መካከል አንዱ በሆነው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ዘርፍ የገጠሩን ማህበረሰብ የትኩረት ማዕከሉ በማድረግ ሲንቀሳቀስ ቆይቷልም ብለዋል።

ድርጅቱ በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት በማሰባሰብ በ 7 ክልሎች በተለይም በአፋር፣ ሶማሌ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች የንጹህ መጠጥ አቅርቦት ስራ ሰርቷልም ተብሏል።

ከተሰሩ ስራዎች መካከልም 37 መለስተኛ የእጅ ፓምፖች፣ 87 ባለ አራት ቦኖዎች፣ 100 ኪሜ የውሃ መስመር ዝርጋታ ስራዎች፣ 185 ሜትር ኪዩብ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች
እና ከ100 በላይ ቤት ለቤት የቧንቧ አገልግሎት መስጠቱ ተገልጿል።

እንዲሁም 1 በፀሃይ ሃይል የሚሰራ ሶላር ፓምፕ እና 4 በነዳጅ የሚሰሩ ጀነሬተሮች
ለንፁህ መጠጥ ውሃ መሰረተ-ልማቶቹ ግንባታ ስራ ላይ በማዋል ከ32 በላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ መሰረተ ልማቶችን መተግበሩን አቶ ከማል ተናግረዋል።

ድርጅቱ የተመሰረተበትን 15ኛ ዓመት መስከረም 11 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ አክብሯል።

ኃላፊው አክለውም በቀጣይ 5 ዓመታትም ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት በማሰባሰብ 500 ሺህ በገጠር የሚኖሩ ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል።

ድርጅቱ በ15 ዓመቱ የልማት ጉዞ ከጎኑ ለነበሩ አጋር ድርጅቶች፣ ለጋሾች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ሌሎች አካላት ምስጋና ያቀረበ ሲሆን ሁሉም ዜጎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ በቀላሉ እስኪያገኙ ድረስ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጥሪ አቅርቧል።

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ከሆነ በኢትዮጵያ ንጹህ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ተደራሽነት 70 በመቶ ሲሆን 60 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ አሁንም የውሀ አቅርቦት ችግር አለበት።

በገጠር ከሚኖረው ህዝብ ውስጥ ንጹህ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት 40 በመቶ ሲሆን በከተሞች ግን 90 በመቶ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶች፣ የመሰረተ ልማት ችግሮች እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች የኢትዮጵያን የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ከሚፈትኑ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *