በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ሀብት ላይ ከተደቀኑ በርካታ ችግሮች መካከል ህገወጥ የእንስሳት ዝውውር አንዱ መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።
በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት ህገወጥ ዝውውር ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳንኤል ጳውሎስ እንደተናገሩት ለተለያዩ አላማዎች ሲባል በኢትዮጵያ የሚገኙ የዱር እንስሳት ከነህይወታቸው በህገወጥ መንገድ ይዘዋወራሉ።
በዚህ መልኩ ከሀገር የሚወጡ እንስሳቶች በርካታ ቢሆኑም በቀዳሚነት አቦሸማኔ ይጠቀሳል ።
አቦሸማኔ በተለይም በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል በሱማሌ ክልል መኖሪያውን በማድረጉ የአካባቢው ማህበረሰቦች ባካበቱት ተፈጥሮአዊ ዘዴ የአቦ ሸማኔ ቡችላዎችን በመያዝ ሶማሌላንድ አካባቢ ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ ተጠቁሟል።
በዚህ መልኩ ይህ እንስሳ ወደ መካከለኛው የአረብ ሀገራት ጭምር ላሉ ባለሀብቶች የሚሸጥበት ሁኔታ መኖሩን የገለፁት አቶ ዳንኤል ግለሰቦቹ የራሳቸው የሆነ መካነ አራዊት ስላላቸው እንስሳቱን የመግዛት ፍላጎታቸው ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።
ወደ መካከለኛው ምስራቅ የአረብ ሀገራት የሚገኙት አቦ ሸማኔዎችም ከአፍሪካ ቀንድ በተለይም ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ ሲሉ ባለሙያው ጨምረው ተናግረዋል።
አቦሸማኔን ጨምሮ ሌሎች እንስሳትን ከህገወጥ ዝውውር ለመታደግና ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን አሁን ላይ በአነፍናፊ ውሾች የታገዘ የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ተብሏል።
በኢትዮጵያ በህገወጥ አድን ምክንያት አንበሳ እና ዋልያ ኢቤክስ እንስሳት የመጥፋት አደጋ እንደተደቀነባቸው ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያ ለሕጋዊ አደን የተፈቀዱ እና ያልተፈቀዱ የዱር እንስሳት ያሏት ሲሆን አንበሳ፣ ነብር፣ የደጋ አጋዘንን ጨምሮ በአጠቃላይ 54 የዱር እንስሳት ለአደን ተፈቅደዋል፡፡
እንዲሁም ዋልያ፣ ዝሆን፣ ተኩላ፣ አውልድጌሳን ጨምሮ 48 የዱር እንስሳት ደግሞ ለአደን ከተከለከሉት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህን የዱር እንስሳት ለማደን ዝቅተኛው 50 ዶላር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 15 ሺህ ዶላር ክፍያን እንደምታስከፍል አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
የመጥፋት አደጋ ተደቅኖበታል የተባለው አንበሳን ለማደን 4 ሺህ 500 ዶላር መክፈል እንደ ግዴታም አስቀምጣለች፡፡