የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል የመንግስት ባለስልጣንን ለመግደል ሞከሩ

እንዲሁም ታጣቂዎቹ የላሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪን እንዳቆሰሉ ቢቢሲ ዘግቧል።

ታጣቂዎች ተቆጣጥረውታል የተባለው አካባቢ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ከተማ እንደሸሹም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳንን ከምትጎራበታቸው ክልሎች አንዱ በሆነው ጋምቤላ ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸም የጀመሩት ከትናንት በስቲያ ከረቡዕ ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ አንድ የላሬ ወረዳ ኃላፊ ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ “የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የገቡት” ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ግጭት ውስጥ ያሉት የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ (Sudan People’s Liberation Movement In Opposition) ታጣቂዎች ናቸው።

ታጣቂዎቹ የገቡት የኑዌር ብሔረሰብ ዞን ላሬ ወረዳ ስር በምትገኘው የድንበር አካባቢዋ ፓጋግ ቀበሌ እንደሆነ ምንጩ ገልጸዋል።

ከሀገሪቱ መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ያሉት ታጣቂዎች ድንበሩን አቋርጠው የገቡት “ተኩስ ሲከፈትባቸው ሸሽተው” እንደሆነም ተናግረዋል።

“ታጣቂዎቹ የራሳቸውን ድንበር ዘለው ወደ እኛ ድንበር ነው የገቡት። እስከ ትናንት [ሐሙስ] ድረስ ያገኘነው መረጃ በእኛ ድንበር [ውስጥ] ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ባንዲራ ጭምር ነው የወሰዱት” ብለዋል።

“ታጣቂዎቹ እስከ ትናንት ድረስ እየገቡ” እንደሆነ መረጃ እንዳላቸውም አክለዋል።
ኃላፊው፤ ታጣቂዎቹ ድንበሩን አቋርጠው ከገቡ በኋላ “በነዋሪዎች ላይ ተኩስ” መክፈታቸውን እና “ቤቶችን ማቃጠላቸውን” ተናግረዋል።

የታጣቂዎቹን እንቅስቃሴ ተከትሎ “ሕዝቡን ለማረጋጋት” እና “ድንበሩን ለመመልከት” ወደ አካባቢው የተጓዙት የላሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቶክ ሞንግ በተከፈተባቸው ጥቃት እንደቆሰሉም ምንጩ ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መረጃም የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ትናንት ሐሙስ ሚያዝያ 23/2017 ዓ.ም. ተኩስ እንደተከፈተባቸው እና “በቀኝ እግራቸው ታፋ ላይ ተመትተው መቁሰላቸውን” አረጋግጧል።

የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ “የመንግሥት አካላት” በአካባቢው የተገኙት በደቡብ ሱዳን የተነሳው “የእርስ እርስ ግጭት” በድንበር አካባቢ በሚገኘው “ፓጋግ ቀበሌ ኩብሪ ቢልኩን ተብሎ ወደ ሚጠራው አካባቢ እየተዛመተ” መሆኑን ለማጣራት እንደነበር ገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *