የአቦል አዳዲስ ይዘቶች ማስተዋወቂያ እና የአፋፍ ቴሌኖቬላ ማጠናቀቂያ ልዩ ዝግጅት ተካሄደ

ሕንድ ለ20 የፊልም ሙያተኞች የስኮላርሽፕ እድል ሰጥታለች

“የአቦል አዳዲስ ይዘቶች ማስተዋወቂያና የአፋፍ ቴሌኖቬላ ማጠናቀቂያ” ልዩ በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት አዳራሽ (ወመዘክር) ተካሂዷል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ ታዋቂ የፊልም ባለሙያዎች፣ ተወናዮች፣ የመንግስት ተቋማት ሃለፊዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመህዲ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር “ዲኤስቲቪ በኢትዮጵያ የፊልም ጥበብ እንዲጎለብት በፋይናንስና በስርጭት እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በርካቶች የፊልም ጥበብ ባለሙያዎች ይህንን በመጠቀም እየተንቀሳቀሱ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም ለዚህ ማሳያ የሆነው ” አፋፍ ተከታታይ ድራማ በፕሮዳክሽን ጥራትም በይዘትም ምሳሌ በሚሆን መልኩ ተዘጋጅቶ ሲቀርብ ነበር” ብለዋል።

በስኬት በመጠናቀቁም የይዘት ባለቤቱን ዲኤስቲቪ አቦል ቴሌቪዥንና አዘጋጁን ሚካኤል ሚሊዮንን ( ሰውኛ ፕሮዳክሽን ) እና አባላቱን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ “ዲኤስቲቪ በስፖርቱ ነው የበለጠ የሚታወቀው ፣ በፊልምና መዝናኛ ይዘቶቹ እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን እንደ ስፖርቱ ማስተዋወቅ ይጠበቅበታልም” ብለዋል።

የመልቲቾይስ (ዲኤስቲቪ) ኢትዮጵያ የሬጉላቶሪና ኮርፖሬት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መታሰቢያ በላይነህ በበኩላቸው የኢትዮጵያን እሴትና ባሕል ጠብቀው የሚዘጋጁ ሀገርኛ የቴሌቪዥን ይዘቶች ከአቦል ቴሌቪዥን ስርጭት መጀመር በኋላ በጥራትና በብዛትም መበራከታቸውን ገልጸዋል።

በአቦልና ማዲ አቦል በተሰኙ የኤምኔት ቻናሎች አማካኝነት በዲኤስቲቪ በአማርኛና አፋን ኦሮሞ የሚተላለፉ ይዘቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት መታሰቢያ በአፋፍ የታየው የቀረጻ መንደር ገንብቶ በጥራት ፕሮዳክሽን መስራት በሌሎችም እንደሚደገም እምነታቸውን ገልፀዋል።

መልቲቾይስ ለሀገርኛ ይዘቶች መጎልበትም አበክሮ ይሰራል ብለዋል። በመድረኩ የእሳት እራት፣ አሻራ፣ የልቤ፣ አላውቅም አናውቅም፣ እሹሩሩ፣ ምሕረት፣ ደማቆቹ፣ እንሞካከር፣ ስፍራሽ ብዙ፣ ሁለት ጓዳ፣ Abbaa Karraa, Killoollee እና Abakara S3 ጨምሮ ሌሎችም እንዲተዋወቁ ተደርጓል።

በተወዳጅነት ለ281 ክፍሎች በሳምንት ለ5 ቀናት ሲተላለፍ የቆየው የአፋፍ ቴሌኖቬላ ሾው ራነር፣ ዳይሬክተርና ተዋናይ ሚካኤል ሚሊዮን በበኩሉ ዲኤስቲቪ በአቦል ቻናል ለኢትዮጵያ የፊልም ባለሙያዎች የፈጠረውን ዕድል አመስግኗል።

አፋፍ በፕሮዳክሽንና በይዘት ጥራት፣ አንጋፋና ወጣቶችን ማቀናጀቱ፣ በሲኒማ ደረጃ ፕሮዲዩስ መደረጉና የቀረፃ ፊልም መንደር ተገንብቶ መሰራቱ ዓይነተኛ ማሳያዎች እንደነበሩ የተናገረው አርቲስቱ በይዘትም በፕሮዳክሽንም ጥራቱንና ተወዳጅነቱን እንደጠበቀ በመጠናቀቁም የቴሌኖቬላውን አባላትና ድጋፍ ያደረጉ አካላት አመስግኗል።

የአቦል አዳዲስ ተከታታይ ድራማዎች አዘጋጆች በመድረኩ ልምዳቸውንና የአቦልን አስተዋፅኦ ያጋሩ ሲሆን ይዘቶቻቸውንም አስተዋውቀዋል።

አንተህ ኃይሌ ስለ “የእሳት እራት” ቴሌኖቬላ፣ ኑር አክመል ስለ “አሻራ” ቴሌኖቬላ፣ ፌቨን ከተማ ስለ “የልቤ” ድራማ እንዲሁም ኡስማን አወል ስለ ማዲ አቦል ይዘቶች ገለፃ አድርገዋል።

የተጠናቀቀው አፋፍ ቴሌኖቬላ አባላትም ስለ ትወና፣ ፕሮዳክሽን ማኔጅመንትና አጠቃላይ ይዘት ልምዳቸውን አጋርተዋል።

የዘንድሮ የጉማ አዋርድ የቴሌቪዥን ተከታታይ ምርጥ ተዋናይት ዘርፍ አሸናፊዋና የአፋፍ መሪ ገፀ ባሕሪይና ፕሮዲዩሰር መዐዛ ታከለ (እስከዳር) በዚሁ መድረክ ተመስግናለች።

በመድረኩ በእንግድነት የተገኙት በኢትዮጵያ የሕንድ ኤምባሲ ም/ሰክረተሪ የሆኑት ሺሪ ራንጅት ኩማር ሕንድ ለኢትዮጵያ ፊልምና ባህል ዕድገት በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን አስታውሰው በአቦል ቴሌቪዥን አማካኝነት እየተዘጋጀ ሲቀርብ ለነበረውና በሰውኛ ፕሮዳክሽን በላቀ ጥራት ለተሰራው አፋፍ ቴሌኖቬላ አድናቆታቸውን ገለፀዋል።

በአፋፍ ለተሳተፉ 20 ባለሙያዎችም በሕንድ የትምህርት ዕድል ለመስጠትም ቃል ገብተዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *