የዘር ፍሬ ልገሳን የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ “የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ” በሚል ርዕስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
አስራ ሁለት ክፍሎች ያሉት ረቂቅ አዋጁ ስለ አጠቃላይ የጤና አገልግሎት፣ ስለ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ፣ ስለ ልዩ የጤና አገልግሎቶች፤ ስለ ጤና ዘርፍ የሰው ኃብት ልማት እና አስተዳደር፤ ስለ ጤና እና ጤና ነክ ተቋማት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ቁጥጥርን የሚመለከቱ 60 አንቀጾች አሉት።
ስለ ልዩ የጤና አገልግሎቶች የሚያወሳው የአዋጁ አራተኛ ክፍል ከዘረዘራቸው የጤና አገልግሎቶች መካከል አንዱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥነ ተዋልዶ ሕክምና አገልግሎት ነው።
በዚህ ንዑስ ክፍል ሥር የተካተተው አንቀጽ “ፈቃድ የተሰጠው የጤና ተቋም በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥነ ተዋልዶ የሕክምና አገልገሎት ሊሰጥ ይችላል” ሲል ሕክምናው በሕግ መፈቀዱን ይደነግጋል።
“የዘርፍ ፍሬ ልገሳ… ከዚህ ቀደም በሕግ የተፈቀደ ተግባር ያልነበረ” መሆኑን የጠቆመው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ፤ በዚህኛው ረቂቅ አዋጅ “ልገሳውን ማከናወን እንደሚቻል የሚደነግግ እና የሚከናወንበትን ሥርዓት የያዘ ዝርዝር ድንጋጌ” መካታቱን አብራርቷል።
ከአስራ አንድ ዓመታት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው “የምግብ፣ መድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር” ደንብ፤ ፈቃድ ያገኙ ተቋማት የሰው ሰራሽ ሕክምና መስጠት እንደሚችሉ ደንግጓል።
የአዋጁ ድንጋጌ “አግባብ ያለው አካል ፈቃድ በሚሰጠው የጤና ተቋም እና የጤና ባለሙያ ሰው ሰራሽ የተዋልዶ ሕክምና መስጠጥ ይቻላል” ይላል።
ደንቡ የዘር ፍሬ ልገሳ ላይ ክለከላን ባያስቀምጥም በግልጽ በሕግ የተፈቀደ መሆኑንም አይጠቅስም።
ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በበኩሉ የዘር ፍሬ ልገሳ ማድረግ እንደሚቻል እና ሂደቱ ምን መሆን እንዳለበት አስፍሯል።
በረቂቁ መሠረት የዘር ፍሬ መሰብሰብ የሚቻለው ለዚሁ ዓላማ በጤና ሚኒስቴር የተለየ ተቋም ብቻ ነው። ማንኛውም ሰው በሚኒስቴሩ ለተለየው ተቋም የዘር ፍሬውን መለገስ እንደሚችል ረቂቅ ላይ ሰፍሯል።
ይህ የአዋጁ ድንጋጌ ቢኖርም ረቂቁ የዘር ፍሬ ከለጋሾች የሚወሰደው “ከፍተኛ ጉዳት የማያስከትልባቸው መሆኑ በሕክምና ሲረጋገጥ ብቻ” መሆኑን አስቀምጧል።
በረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ከተቀመጠው አግባብ ውጪ “የዘር ፍሬ መለገስ፣ መሰብሰብ ወይም መሸጥ” የተከለከለ መሆኑ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።
የዘር ፍሬ ለመሰብሰብ ከተፈቀደለት ተቋም በተገኘ የዘር ፍሬ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥነ-ተዋልዶ ሕክምና አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው ተገልጋዮች ሊሰጥ እንደሚችል ረቂቅ አዋጁ ያትታል።
ረቂቁ አክሎም በዚህ የሕክምና አገልግሎት “ልጅ ያገኙ ባለትዳሮች የሚወለደው ልጅ ሕጋዊ ወላጆች ይሆናሉ” ይላል።
በረቂቅ አዋጁ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥነ ተዋልዶ ሕክምና አገልግሎት ሊሰጥ የሚችለው በአራት ሁኔታዎች ብቻ መሆኑን ያስቀምጣል።
በረቂቅ አዋጁ መሠረት የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በሕጋዊ ጋብቻ የተጣመሩ እና ለዚህም ከሚመለከተው አካል ማረጋገጫ ማቅረብ አለባቸው።
ሌላኛው አስገዳጅ ሁኔታ “ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ልጅ መውለድ የማይችሉ መሆኑ በዘርፉ ባለሙያ ሲረጋገጥ” መሆኑ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።
የሚሰጠው ሕክምና አወንታዊ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል እና በተገልጋዩ ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል መሆኑ በሕክምና ባለሙያ መረጋገጥ አለበት።
አራተኛው እና የመጨረሻው ቅደመ ሁኔታ ደግሞ የባለትዳሮቹን “አገልግሎቱን ለማግኘት በመረጃ ላይ የተመሠረተ የጽሁፍ ፈቃድ” የሚጠይቅ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ባለትዳሮቹ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ልጅ መውለድ ቢችሉም፤ “መውለዳቸው በጤናቸው ላይ ከባድ እክል የሚያስከትል መሆኑ በባለሙያ ከተረጋገጠ” ሕክምናውን ማግኘት እንደሚችሉ ረቂቁ ላይ መስፈሩን ቢቢሲ ዘግቧል።
ረቂቅ አዋጁ፤ “የዘር ፍሬ ወይም ከማህፀን ውጪ የተዘጋጀ የዘር ፍሬ ውህድ ወደ ሴቷ ማህጸን ከመግባቱ በፊት በባለሙያ ውሳኔ ወይም በባለ ትዳሮቹ ፍላጎት በማንኛውም ጊዜ ሊወገድ ይችላል” የሚል ድንጋጌን አካትቷል።
ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ እንዲወገድ የተወሰነው የዘር ፍሬ ወይም ዘርፍ ፍሬ ውሃ “ከተገልጋዮች ፍቃድ ከተገኘ ለምርምር ዓላማ ሊውል ይችላል” ይላል።
የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ “በዘር ፍሬ ልገሳ ሥርዓት የሚወለዱ ልጆች እና ወላጆችን በተመለከተ የፌደራል ቤተሰብ ሕግ ላይ ከተቀመጠው የተለየ በመሆኑ ይህንኑ ልዩነት ከቤተሰብ ሕጉ ጋር ባልተፋለሰ መልኩ እንዲቀመጥ ተደርጓል” ይላል።
ተፈጻሚነት የሌላቸውን ሕጎች የሚዘረዝረው የረቂቁ ክፍል በቤተሰብ ሕግ አዋጁ “ስለመወለድ የሚደነግጉት የአዋጁ … ድንጋጌዎች በዘር ፍሬ ልገሳ በተገኙ ልጆች እና ወላጆቻቸው ላይ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም” ሲል ይደነግጋል።
ተፈጻሚነት አይኖራቸውም የተባሉት ድንጋጌዎች አባትነትን እና እናትነትን ስለማወቅ፣ ልጅነትን ስለመቀበል፣ ስለ ልጅነት ማስረጃ እና ሌሎች ጉዳዮችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ናቸው።