በአዲስ አበባ የጉበት ንቅለ ተከላ ህክምና ማዕከል ሊማቋቋም ነው

በኢትዮጵያ የጉበት ንቅለ ተከላ ፕሮግራም በትብብር ለማቋቋም የሚያስችል ስምምነት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ በጤና ሚኒስቴር እና በካሊፎርኒያ ፓሲፊክ የሕክምና ማዕከል መካከል ተፈርሟል።

ይህ ተነሳሽነት በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ዶ/ር ቅድስት ኪዳኔ ይማም የሚመራ ሲሆን በሰሜን ካሊፎርኒያ ያሉ ባልደረቦቻቸውን በማስተባበር ወደ ተግባር የተቀየረ ነው።

ከዚህ ቀደም ዶ/ር ቅድስት አገልግሎቱን በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል የጉበት ንቅለ ተከላ ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያስችል የህክምና ክፍል ለመመስረት የሙያ ስልጠናዎች እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ ሄፐታይተስ ቢ እና ሄፐታይተስ ሲ በተሰኙት የጉበት በሽታ ተጠቂዎች ከፍተኛ ከሆነባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን የዓለም ጤና ድርጅት ከሶት ወራት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጉበት፣ ቆሽትና የሀሞት ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ውለታው ጫኔ በዚህ ዙሪያ የተሰራው ሀገራዊ የዳሰሳ ጥናት በሽታው በስፋት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር ውለታው ገለጻ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር ውስጥ 9.4 በመቶ የሚሆነው ሄፐታይተስ ቢ እንዲሁም 3.7 በመቶ የሚሆነው ደግሞ የሄፐታይተስ ሲ ተጠቂ ናቸው።

አክለውም የጉበት ጠባሳ ሆኖባቸው ወደ ጉበት ካንሰር የተለወጠባቸው እና በሆስፒታሉ ህክምና ከወሰዱት ውስጥ 50 በመቶ ምክንያቱ ሄፐታይተስ ቢ እና ሄፐታይተስ ሲ ነው ያሉ ሲሆን 50 በመቶ ግን ከዚህ ውጪ ያለ ምክንያት እንደሆነ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ በጉበት በሽታ ተጠቂዎች ልክ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ የጤና መሰረተ ልማት አለመኖሩ ከፍተኛ ክፍተት የፈጠረ ሲሆን ይህንን ህክምና ለማግኘት ወደ ውጪ የሚሄዱ ታካሚዎች ለህክምና ብቻ እስከ 5 ሚሊዮን ብር ሊያወጡ ይችላሉ።

አዲ የሚቋቋመው ይህ የጉበት ንቅለ ተከላ ህክምና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ታካሚዎች ወጪያቸው እስከ 2 ሚሊዮን ብር ሊቀንስ ሊወርድ እንደሚችል ዶ/ር ውለታው ጠቁመዋል።

ዶ/ር ቅድስት የጉበት ንቅለ ተከላ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ለመጀመር ለ10 ዓመታት ሲሰሩበት እንደቆዩ ገልጸው፤ በቅርቡም ከሌሎች የሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት መሰል ህክምናዎችን ሰጥተው ተመልሰዋል። በተጨማሪም ለሆስፒታሉ 35ሺ ዶላር የሚያወጣ ድጋፍም አበርክተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባሳለፍነው ግንቦት ላይ የጉበት በሽታ ጉባኤውን በፖርቹጋል ባካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው በዓለማችን በየዕለቱ 3 ሺህ 500 ሰዎች በጉበት በሽታ እየሞቱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት የኤችአይቪ፣ ሄፓ ታይተስ እና ተላላፊ በሽታዎች ፕሮግራም ሃላፊ ሜግ ዶሂርቴ እንዳሉት በጉበት በሽታ ከሚሞቱት ውስጥ 83 በመቶዎቹ በሄፓታይተስ ቢ በተሰኘው የጉበት በሽታ የሚሞቱ ናቸው ብለዋል፡፡

በጉበት በሽታ የሚጠቁ ዜጎች እየጨመረ ነው ያሉት ሃላፊው 63 በመቶ ያህሉ ተጠቂዎች በአፍሪካ የሚገኙ ዜጎች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

በየዕለቱ ስድስት ሺህ ሰዎች በጉበት በሽታ እየተጠቁ ነው ያለው የዓለም ጤና ድርጅት ተጠቂዎች በቂ ህክምና እያገኙ እንዳልሆነም አስታውቋል፡፡

በሽታው ከተስፋፋባቸው ሀገራት መካከል 75 በመቶ ያህሉ ሽታው እየተስፋፋባቸው ካሉ የዓለማችን ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ቻይና፣ ባንግላዲሽ፣ ናይጀሪያ፣ሕንድ እና ኢንዶኔዢያ ተጠቅሰዋል፡፡

በ187 ሀገራት በተጠና ጥናት መሰረትም የጉበት በሽታ በየዓመቱ እየጨመረ እንደሆነም የተገለጸ ሲሆን ከጠቅላላው ተጠቂዎች ውስጥ መድሃኒት እያገኙ ያሉት ሶስት በመቶዎቹ ብቻ ናቸውም ብሏል፡፡

በአፍሪካ ከሚወለዱ አምስት ህጻናት መካከል አንዱ ብቻ የጉበት በሽታ መከላከያ ክትባት እንደሚወስዱም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *