መንግስት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ፍትህ እንዲያገኙ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር ጠይቋል።
ማህበሩ የጋዜጠኞቹ የፍርድ ሂደትም ከፖለቲካ አተያይ በፀዳ መንገድ እንዲሆን ጥሪውን ያቀርባል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር አዲስ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በአዲ አበባ ቃሊቲና ቂሊንጦ ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም ስለ ማረሚያ ቤት አያያዝ እና አጠቃላይ የፍትህ ሂደቱ ያለበትን ሁኔታ ከጋዜጠኞቹ ጋር እንደተወያዩ ማህበሩ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡
ጋዜጠኞቹ በማረሚያ ቤቶቹ አያያዝ በኩል ቅሬታ ባይኖራቸውም በፖሊስ ቁጥጥር ስር በተያዙበት ወቅት የተያዙበት መንገድም ሆነ ከተያዙ በኃላ ያለው የፍርድ ቤት ሂደት አግባብነት እንደሚጎድለው ተናግረዋል፡፡
በሁለቱም ማረሚያ ቤቶች ከአንድ ዓመት በላይ ሳይፈረድባቸው የታሰሩ ጋዜጠኞች መኖራቸውን ማኅበሩ እንዳረጋገጠ አስታውቋል።
ስለሆነም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንዲሁም የሚዲያ ምህዳሩ ነፃ እንዲሆን የሚመለከታቸወን አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማህበሩ ጠይቋል።
አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ተቀዛቅዞ የቆየውን የማኅበሩን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለማስቀጠል አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ለመንቀሳቀስም ውይይት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በአጭር ጊዜ እቅድ ተቀዛቅዞ የቆየውን የአባላት ተሳትፎ ለማሳደግ ነባር አባላትን ማነቃቃት እና የአዳዲስ አባላትን ምዝገባ እንደ አዲስ ጀምሯል።
ከአባላት ማፍራት እና ማነቃቃት በተጨማሪ ማኅበሩ ከዚህ ቀደም በንቃት ይሰራቸው የነበሩና ለሙያው ማደግ ሚና ያላቸውን ተግባራትንም ለማከናወን ዕቅድ ይዞ ወደ ተግባር ገብቻለሁ ብሏል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር በዋነኛነት የጋዜጠኞችን መብትና ክብር ለማስጠበቅ በሚል የተቋቋመ የሙያ ማህበር ነው።
ሙያው ከአገራችን የፖለቲካ ምስቅልቅል ሁኔታ ጋር አብሮ ፈተና ውስጥ የገባ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ የፖለቲካ ምህዳሩ የፈጠራቸው የጋዜጠኞች አስር ፣ ስደትና ውክብያ የወቅቱ የባለሙያው ትልቅ ፈተና መሆኑን ማህበሩ ገልጿል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር ችግር ላይ የወደቀውን የጋዜጠኞችን ደህንነትና ሙያዊ ነፃነት ለማስከበር እንደሚሰራ አስታውቋል።
በዚህ አጋጣሚ ማኅበሩ በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች አባል ሁነው እንዲመዘገቡና ማህበሩን በማጠናከር ለሙያው መከበር ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ድምፅ እንዲሆኑም ጥሪውን አቅርቧል።