በዓለም አቀፉ የሴቶች ሰላም ቡድን አዘጋጅነት የተካሄደው ይህ የፍቅር እና ሰላም ኪነ ጥበብ ውድድር በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ዋናው ግቢ ውስጥ ተካሂዷል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የስዕል፣ ግጥም እና ሌሎች የስነ ጽሁፍ ይዘቶችን ለተመልካቾች አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ እና ተስፋዎች ላይ ያተኮረው ይህ የኪነ ጥበብ ውድድር ህጻናት እና ታዳጊዎች የኪነ ትበብ ስራዎቻቸውን ለተመልካቾች አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ስርዓተ ጾታ ሃላፊ ሰውዓለም ጸጋ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ ሰላም ከራቃት ዓመታትን እንዳስቆጠረች ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ላጋጠማት የሰላም ችግር ዋነኛ መንስኤው የሴቶች በግጭት አፈታት ዙሪያ ያላቸው ተሳትፎ አናሳ በመሆኑ ነው ያሉት ሰውዓለም ጸጋ በጦርነት እና ግጭቶች የበለጠ ተጎጂዎች ህጻናት እና ሴቶች ናቸውም ብለዋል፡፡
ሰላማችን ወደ ነበረበት እንዲመለስ ሴቶች በሚገባ ስለ ሰላም መስራት እና ሴቶችን የበለጠ ተሳታፊ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የሴቶች ሰላም ቡድን ተጠሪ የሆኑት ኢስተር ኪም በበኩላቸው በመላው ዓለም የተካሄዱ ጦርነቶች እና የሰላም ችግሮች በዋነኛነት የሚጎዱት ሴቶችን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሴቶች ለሰላም ግንባታ የበለጠ ቢሳተፉ ዓለማችን የተሻለ ሰላም ይኖራት ነበር ያሉት ኢስተር ኪም ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው ሴቶች ስለ ሰላም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ደቡብ ኮሪያ በታሪኳ ከባድ ጦርነት አሳልፋለች ያሉት ኢስተር ይህ ጦርነት ሴቶችን እና ህጻናትን የበለጠ ጎድቶ እንዳለፈ ተናግረው በኢትዮጵያም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሴቶች እና ህጻናት ሰላማቸውን እንዲጠብቁ ማስተማራችንን እንቀጥላልን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች ሰላም ቡድን መሰረቱን ደቡብ ኮሪያ ሴኡል በማድረግ ከ173 ሀገራት የተውጣጡ ከ700 ሺህ በላይ አባላት ያሉት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡
ድርጅቱ በግጭቶች እና ጦርነቶች የበለጠ ተጎጂ የሆኑት ሴቶችን ማዕከል በማድረግ የተቋቋመ ሲሆን ሴቶች እና ህጻናትን በመጠቀም ስለ ሰላም አስፈላጊነት የሚሰራ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡