በርበራ ወደብ በዓለም ባንክ የጥራት መመዘኛ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ተመረጠ

የዓለም ባንክ በመላው ዓለም ያሉ ወደቦች እቃ የመጫን አቅማቸውን የተመለከተ አሁናዊ ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡

የእቃ ጫኝ ኮንቴይነር የመያዝ አቅማቸውን መሰረት በማድረግ የወደቦችን ደረጃ ያወጣው ባንኩ ኢትዮጵያ የባህር ሀይሏን ልታቋቁምበት ያሰበችበት በርበራ የተሻለ ደረጃን አግኝቷል፡፡

በባንኩ ሪፖርት መሰረት የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ንብረት የሆነው በርበራ ወደብ ከሰሃራ በረሃ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የመጀመሪያው ወደብ ተብሏል፡፡

በርበራ ወደብ በዓለም ካሉ ወደቦች በ103ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ ቀዳሚው ሆኗል፡፡

ሞቃዲሾ ወደብ ከበርበራ ወደብ በመቀጠል በሁለተኝነት ሲጠቀስ የጊኒው ኮናክሪ በሶስተኝነት ሲቀመጥ  የኢኳቶሪያል ጊኒው ማለቡ ወደብ ደግሞ በአራተኝነት ተቀምጧል፡፡

ከመላው ዓለም ደግሞ የቻይናው ያንግሻህ ወደብ በአንደኝነት ሲቀመጥ የኦማኑ ሳላላህ ደግሞ ሁለተኛ እንዲሁም የኮሎምቢያው ካርታግና ወደብ ሶስተኛ ሆኗል፡፡

ከመላው አፍሪካ የሞሮኮ፣ አልጀሪያ እና ግብጽ ወደቦች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃዎች ይዘዋል ሲል ባንኩ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት የወደብ አማራጮችን ስታማትር የቆየች ሲሆን በርበራ ወደብን ለመጠቀም መንገድን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ስትገነባ መቆየቷ ይታወሳል፡፡

ከንግድ ባለፈም ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ በበርበራ ወደብ ላይ የባህር ሀይሏን ማስፈር የሚያስችላትን ስምምነት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ተፈራርማለች፡፡

ስምምነቱን ተከትሎ ሶማሊላድን እንደ ራሷ ግዛት የምታያት ሶማሊያ ተቃውሞዋን በይፋ እና በተለያዩ መንገዶች በመግለጽ ላይ ስትሆን ኢትዮጵያ ስምምነቱን በይፋ እንደሰረዘች ካልገለጸች በስተቀር የፊት ለፊት ውይይት እንደማታደርግ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *