ፖለቲከኛው የሺዋስ አሰፋ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ትናንት ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት አንድ ሰዓት ካዛንቺስ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አብርሃም ሃይማኖት ለአሻም እንዳሉት የሺዋስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህዳር 30 ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ውስጥ አንደኛው የሆኑት ናትናዔል መኮንን በዛሬው እለት ከእስር ተፈቷል።
የሺዋስ አሰፋ የህዳር 30 ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ሲሆኑ ሰልፉ ከመካሄዱ ሦስት ቀናት በፊት (ህዳር 27) ከአስተባባሪዎቹ መካከል አብርሃም ሃይማኖት፣ ጊደና መድህን፣ ናትናዔል መኮንንን ጨምሮ ሌሎች ፖለቲከኞችና የህግ ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ አቶ የሺዋስ ግን አልታሰሩም ነበር።
ህዳር 27 በቁጥጥር ስር የዋሉት አስተባባሪዎቹ አራት ወራት ገደማ ከተጠጋ የአዋሽ አርባ እስር በኋላ ሲፈቱ ናትናዔል መኮንን ግን እስካዛሬ ድረስ ቆይተው ተፈተዋል።
ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል የኢህአፓ ፕርዝዳንት ዝናቡ አበራ በቁጥጥር ስር ውለው፣ በአዋሽ አርባ በእስር ላይ እንደሚገኙ አሻም ቲቪ ዘግቧል።
ትናንት በቁጥጥር ስር የዋሉት ዕውቁ ፖለቲከኛ የሺዋስ አሰፋ ኢዜማን ከለቀቁ በኋላ አሻም ቲቪን ጨምሮ በተለያዩ ብዙሃን መገናኛ ምልከታቸውን ከማጋራት ውጪ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ተሳትፎ ስለማድረጋቸው የሚያመላክት ፍንጭ የለም።
ይሁንና ይህ ዘገባ እስከተሰራበት ጊዜ ድረስ የመንግስት ተቋም አቶ የሺዋስ አሰፋ ስለመታሰራቸው ያለው ነገር የለም፡፡
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን “መልሼ አደራጃለሁ” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።
ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአማራ ክልል የታወጀ ቢሆንም አዋጁ በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጸመ ነው በሚል የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ፖለቲከኞችን እና ጋዜጠኞችን ለእስር እየዳረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
እንደ እነዚህ ተቋማት ሪፖርት ከሆነ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ዜጎችን ለጅምላ እስር፣ አስገድዶ መሰወር፣ ከህግ ውጪ ግድያ እና ሌሎች ጥሰቶችን እያደረሱ ነው በሚል ጠቅሰዋል፡፡
ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን ይህ አዋጅ ሊጠናቀቅ ሶስት ሳምንታት ቀርቶታል።
በአማራ ክልል በተደጋጋሚ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና ምዕራባዊያን ሀገራት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ጠቅሰዋል፡፡