ኢትዮጵያ በሀርጌሳ ያለው የቆንስላ ጽህፈት ቤቷን ወደ ኤምባሲ አሳደገች

ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ፣ ሃርጌሳ የሚገኘውን የቆንስላ ጽህፈት ቤቷን ሙሉ አገልግሎት ወደሚሰጥ ኤምባሲ ማሳደጓን የሶማሊላንድ ሚኒስትር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከአራት ወራት በፊት በወደብ ጉዳይ በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት እንድትሆን ሶማሊላንድ ደግሞ የሀገርነት እውቅና እንድታገኝ የሚያደርግ በመሆኑ ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣንና እና ተቃውሞን አስከትሏል።

ከአንድ ወር በፊት ሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደርን በ72 ሰዓት ውስጥ ሞቃዲሾን ለቀው እንዲወጡ እና በሀርጌሳ እና ጋሮዌ ያሉ የቆንሱላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ ሰራተኞቹም በሁለት ሳምንት ውስጥ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ መወሰኗን አስታውቃ ነበር፡፡

በወቅቱም ራስ ገዟ ሶማላንድ እና ፑንት ላንድ የሶማሊያ መንግስት በሀርጌሳ እና ጋሮዌ የሚገኙ ቆንስላዎች እንዲዘጉ ያሳለፈውን ውሳኔ መቃወማቸው አይዘነጋም።

የሶማሊላንድ የመረጃ፣ የባህል እና የብሔራዊ መመሪያ ሚኒስትር አሊ ሐሰን መሐመድ (አሊ ማርሃን) ለቢቢሲ ሶማሊኛ ከቀናት በፊት ራሷን በነጻ አገርነት ያወጀችው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ ቆንስላው ወደ ኤምባሲ ማደጉን አስመልክቶ የተናገሩትን አረጋግጠዋል።

“የኢትዮጵያ የቆንስላ ጽህፈት ቤት ሙሉ አገልግሎት ወደሚሰጥ ኤምባሲ ማደጉን አስመልክቶ ከፍተኛ ስፍራ በሚሰጠው ዕለት ፕሬዝዳንቱ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ ሶማሊላንድ ነጻነቷን በማወጅ እንደ አገር የተመሠረተችበትን 33ኛ ዓመት ስታከብር ሃርጌሳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ወደ ኤምባሲ ማደጉን ለመጀመሪያ ጊዜ መናገራቸውን በሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መረጃ ያስረዳል።

የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት የሰጡትን መረጃ አስመልክቶ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሶማሊያ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ያሉት ነገር የለም፡፡

ሶማሊያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ አረብ ሊግ እና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ወይም ኢጋድ በዚህ ስምምነት ዙሪያ እንዲወያዩ እና ውሳኔ እንዲያሳልፉ ጥያቄ አቅርባለች፡፡

ተመድን ጨምሮ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የገቡበትን ግጭት በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡

ሶማሊያ የባህር በሯን በቱርክ ለማስጠበቅ በሚል ወታደራዊ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን በዚህ ስምምነት መሰረትም ቱርክ የሶማሊን ባህር ትጠብቃለች፡፡

ኢትዮጵያ የሶማሊያ እና ቱርክ ስምምነት ዙሪያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ለመፈጸም እንቅፋት አይፈጥርም በሚል ለቀረበው ጥያቄ የሁለቱ ሀገራት ስምምነት አያሳስበኝም ብላለች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም እንዳሉት ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንዳላት፣ ቱርክ እና ሶማሊያ ሉዓላዊ ሀገራት በመሆናቸው የፈለጉትን ስምምነት ከየትኛውም ሀገር ጋር የማድረግ መብት አላቸው ብለዋል፡፡

የሶማሊያ እና ቱርክ ወታደራዊ ስምምነት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ እንዳልሆነም አምባሳደር መለስ ዓለም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *