የቢል እና ሜሊንዳ ጌት ሥራ አስኪያጅ ማርክ ሱዝማን ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ሥራ አስኪያጅ ማርክ ሱዝማን ከሚያዚያ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ መሆኑን አስታወቁ፡፡

ስራ አስኪያጁ ለአንድ ሳምንት በሚያደርጉት ጉብኝት በጤና ነክ ተግዳሮቶች ላይ ለመምከርና ለኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚቀርፉ እድሎችን ለማመቻቸት ይሠራሉ ተብሏል።

ጉብኝቱ የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ከመሪዎችና ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት ሆኖ በመሥራት በመላው አፍሪካ ያሉ ዜጎችን ኑሮ መሻሻል የሚያፋጥኑ መፍትሔዎችን ለመደገፍ እያሳየ ያለው ቆራጥነት አካል ነው።

በዚህ ጉብኝት ወቅት፤ ሱዝማን የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ ለጋሽ ድርጅቶችን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖችን፣ የሳይንስ ሰዎችን፣ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን፣ በቦታው ተገኝተው የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎችንና እና የፈጠራ ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያየ ዘርፍ ላይ ከሚገኙ ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

በነዚህ ውይይቶች ወቅት ሱዝማን አጋሮቻቸው በጤና፣ በግብርናው መስክ፣ በጾታ እኩልነት፣ እና በፋይናንሺያል አካታችነት ዙሪያ በሚሠሯቸው ሥራዎች ላይ ስለገጠሟቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎችና መልካም አጋጣሚዎች በጥልቀት ተረድተው ከሀገር ውስጥ አጋሮች ጋር ግንኙነታቸውን በመፍጠርና ግንኙነቶቹን በማጠናከር ኢትዮጵያ የጤና እና የልማት መሰናክሎችን ተሻግራ ለማለፍ በምታደርገው ጥረት የፋውንዴሽኑን ዘላቂነት ያለው ድጋፍ የበለጠ ያጠናክራሉ።

ፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር በመናበብ በተለይም የእናትና የልጅን ጤንነት ጨምሮ በጾታዊ ጉዳዮች እንዲሁም በትምህርት፣ በግብርና፣ በምርታማነት፣ በፋይናንሺያል አካታችነት እና በነጽህና አጠባበቅ ላይ እየሰራ ይገኛል።

የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ለአፍሪካ ዋና ዋና ችግሮች መፍትሔያቸውም ከአፍሪካ ይመጣል ብሎ እንደሚያምን የገለጸ ሲሆን ለዚህም ነው ፋውንዴሽኑ  በደፋር ሀሳቦቻቸውና ፈጠራ በታከለበት አሠራራቸው በመላው የአህጉሪቱ ክፍል ሕይወት የማዳን፣ የጤና ሁኔታን የማሻሻል እና የተለያዩ ቤተሰቦችን የማገዝ ዐቅም ያላቸው አፍሪካውያን አጋሮቹን እያገዘ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ፋውንዴሽኑ እ.ኤ.አ. እስከ 2026 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ረሀብን፣ በሽታን፣ ጾታዊ አለመመጣጠኖችን እና ድህነትን ለመታገል የሚረዱ አዳዲስ አሠራሮችን ለመፍጠርና ለመተግበር እየሠሩ ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራትና ተቋማት እርዳታ የሚውል ከ7 ቢሊየን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ መድቦ እየሠራ ይገኛል።

ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም 2000 ጀምሮ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ እርዳታውን ያደረገው ይህ ተቋም በ2012 ቢሮውን በአዲስ አበባ ከከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከለጋሾች፣ ከግሉ ሴክተር እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን ድህነት ባጠቃቸው አካባቢዎች የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፋውንዴሽኑ መስራች ለሆኑት ቢል ጌት በ2006 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *