በትግራይ ክልል ጦርነት የቆመ ቢሆንም ከጫፍ ጫፍ ተንቀሳቅሶ መስራት አደጋች ሆኗል ተብሏል፡፡
በክልሉ ከመልካም አስተዳድር ጥያቄዎች ይልቅ የምግብ ጉዳይ ዋነኛው ችግር እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት በቆየው ጦርነት ምክንት ስራ አቁሞ ከነበሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠበቃ ተቋም መቀሌ ቀርንጫፍ አንዱ ነበር፡፡
ይህ ጦርነት በደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በተደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ጦርነቱ የቆመ ሲሆን አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ዳግም ስራ ጀምረዋል፡፡
ከታህሳስ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሥራውን በአዲስ መልክ የጀመረው የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም መቀሌ ቅርንጫፍ በበጀት እጥረት ምክንያት ጉዳዮችን ለመመልከት አዳጋች እየሆነበት እንደመጣ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ደጋፊት ረዳ ለኢትዮ ነጋሪ ተናግረዋል።
ተወካይዋ እንዳሉት ተቋሙ በዋናነት የአስተዳደር በደል የፈፀሙ አካላትን የመቆጣጠርና የመከላከል ብሎም የማስተካከል ሥራ እንደሚሠራ አንስተው ይህንን ሥራቸውን ተደራሽ ለማድረግ የበጀት እጥረት ፈተና እንደሆነባቸው ገልፀዋል።
ከዛ በተጨማሪም ከጦርነቱ በኋላ የተፈጠረው የኃላፊዎች መቀያየር ችግር እንደፈጠረም ሃላፊዋ አንስተዋል። አሁን ላይ ጦርነቱ ቆሞ ሰላም ቢሆንም ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ግን የጸጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ መንቀሳቀስ አዳጋች እንደሆነ ኃላፊዋ ገልጸዋል።
በ2015 ዓ/ም ላይ ከደሞዝ ውጪ ያለምንም በጀት እየሠሩ እንደነበርና በ2016 ዓ/ም ትንሽ በጀት በመመደቡ ለመንቀሳቀስ ተችሏል ያም ሆኖ ግን የአቅም ውስንነት ስላለ የተፈለገውን እና የሚገባውን ያህል ለመዳረስ አልተቻለም ሲልም አክለዋል ።
ከዚህ ባለፈም በክልሉ ውስጥ ያለው ረሀብ ሰዎች መሰረታዊ ነገር ከሆነው ምግብ ውጪ አስተዳደራዊ በደል ተፈጽሞብኛል ብሎ ቅሬታ ለማቅረብ አመቺ ሁኔታ ላይ አይደሉም ያሉን ሃላፊዋ ለዚህም ማሳያ እንዲሆን ተቋሙ በስድስት ወር ውስጥ 174 ቅሬታዎችን ለመቀበል አቅዶ የነበረ ቢሆንም የተቀበለው ግን 50 ቅሬታዎችን ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከነዚህ 50 ቅሬታ አቅራቢዎች መካከልም 25ቱ በመረጃ እጥረት ምክንያት ተቋሙ የማይመለከተውን እና ከተቋሙ ውጪ የሆኑ ማለትም ፍርድ ቤት ያየው የግል በደል እና ወንጀል ነክ የሆኑ ጉዳዮችን ይዘው የመጡ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ለተቋሙ ከቀረቡ 25 ቅሬታዎች ውስጥ የ15ቱ ጉዳይ የውሳኔ ሓሳብ ሲሰጥባቸው 10 ባለጉዳዮች ደግሞ በሒደት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።
የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በትግራይና አማራ ክልሎች 400 የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን እንዲሁም 21 ህጻናት ደግሞ ህይወታቸው አልፎ መወለዳቸውን አረጋግጫለሁ ሲል መናገሩ ይታወሳል።