ስታንዳርድ ባንክ በኢትዮጵያ መሰማራት እንደሚፈልግ ገለጸ

ዋና መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገው ስታንዳርድ ባንክ በአፍሪካ ትልቁን ያልተነካ ገበያ እየፈለገ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት የባንክ ፍቃድ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከሁለት ሳምንት በኃላ የኢንቨስትመንት የባንክ ፍቃድ ማመልከቻዎችን እንደሚቀበል ከቀናት በፊት መግለፁ አይዘነጋም ።

ለዉጪ ፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንኮች ሆነው እንዲመዘገቡ የቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ ፍቃደኝነቱን በማሳየት “ስታንደርድ ባንክ” ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፍ ችሏል።

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንክ ፍቃድ ለማግኘት ዝቅተኛው የተከፈለ ካፒታል ለዉጪ ባንኮች 100 ሚሊዮን ብር እና ከባንክ ላልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት 25 ሚሊዮን ብር ሀብት ሊኖራቸው ይገባል።

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች አምስት የሚደርሱ የባንክ ፈቃድ ለመስጠት ማቀዷን ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ በወቅቱ እንዳሉት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባንኮች እና ባለሀብቶች የባንክ ፈቃድ እንደሚሰጥ ተናግረው ነበር፡፡

ይህም የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ አገልግሎት ለውጭ ተፎካካሪዎች ክፍት ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

እስካሁን የኢትዮጵያ ባንክ ዘርፍ ለውጭ አገራት መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች ዝግ ሆኖ የቆየ ሲሆን፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ግን ለውጭ አገራት ተፎካካሪዎች ክፍት ይደረጋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የውጭ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፉም ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በጋራ የሚሰሩበት አማራጭ ሊኖር እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡

የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በባንክ፣ በቴሌኮም፣ በትራንስፖርት እና አቬሽን ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ካሳዩ ቆይተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለውጭ ኢንቨስተሮች ዝግ ተደርገው የቆዩ ዘርፎች ክፍ እንደሚደረጉ ቃል የገቡ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የውጭ ቴሌኮም ፈቃድ ማግኘቱም ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም የመንግሥት የልማት ድርጅት እና ብቸኛ የቴሌኮም ድርጅት ሆኖ የቆየውን የኢትዮ ቴሌኮም 45 በመቶ ድርሻ ለውጭ ባለሀብት በመሸጥ ሦስተኛ የውጭ ቴሌኮም ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ቢወጣም ተወዳዳሪ በመጥፋቱ ጨረታው ቀርቷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *