በቮልስ ዋገን አይዲ ሲሪየስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ወደ ሀገር እንዳይገቡ ተጥሎ የነበረው እገዳ መነሳቱ ተገልጿል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ ቮልስ ዋገን አይዲ ሲሪየስ (ID Series) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ እገዳ ጥላ ነበር፡፡
ከቻይና ተገጣጥሞ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረው የጀርመን ምርት የሆነው ቮልስ ዋገን ተሽከርካሪ ባትሪው ከኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጋር የሚጣጣም አይደለም በሚል በቀረበው ቅሬታ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ታግዶ ቆይቷል፡፡
በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪና ተሽከርካሪ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አበራ ሞሲሳ እንዳሉት፤ የጀርመን መንግሥት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ቮልስ ዋገን ተሽከርካሪ እንዳይገባ ተደርጎ ቆይቷል፡፡
ደብዳቤው የተሽከርካሪዎች ባትሪ ከኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጋር የማይጣጣም እንዲሁም የጀርመን መንግሥት ለኢትዮጵያ ፈቃድ አልሰጠም የሚል እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በዚህም መሠረት ከባትሪው ጋር ተያይዞ የቀረበውን አቤቱታ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በማስጠናት፤ ባትሪው ምንም ችግር የሌለበትና ለኢትዮጵያ የአየር ንብረትም ተስማሚ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
በተሽከርካሪው ላይ ያለው ባትሪ ሙቀት በሙሊት ጊዜ ከዜሮ እስከ 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዲሁም በሥራ /ዲስቻርጂንግ/ ወቅት ከ20 እስከ 60 ዲግሪ ሴንቲግሬድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህ የሙቀት መጠን ላይ ያለ ባትሪ ጥሩ የሚባልና በኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ ለመሥራትም ምንም ዓይነት ችግር የማይፈጥር መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
የቮልስ ዋገን ተሽከርካሪ ፈሳሽ የባትሪ ሙቀት መቆጣጠሪያ የሚጠቀም በመሆኑ ከሌሎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በተሻለ በተለያዩ የአየር ንብረት ሁኔታ የመሥራት አቅም እንዳላቸውም አብራርተዋል።
በመሆኑም ተሸከርካሪ አስመጪዎች ሕጋዊውን አሠራር ተከትለው የቮልስ ዋገን ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ማስገባት ይችላሉ ብለዋል፡፡
በቻይና የሚገጣጠሙ እነዚህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከሀገራችን የአምራች ቀጥታ ተወካይ እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም የተሽከርካሪዎቹ አስመጪዎች ሙሉ መረጃና ዋስትና መኖሩን ማረጋገጥ ይገባቸዋል ብለዋል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ውጤት መሠረት አገልግሎት የተጀመረ በመሆኑ፤ እነዚህን ክፍተቶች ማሟላት የሚችል አስመጪ ድርጅት የማስገቢያ ፈቃዱን መውሰድ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
መንግስት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲመረቱ፣ እንዲገጣጠሙና ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ለይቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች የአየር ብክለት እያደረሱ ነው በሚል በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በአነስተኛ ግብር ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያበረታታ ህግ በቅርቡ ማጽደቋ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዓመታት ውስጥ ከ150 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ማቀዷ ይታወሳል፡፡