በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠየቀ።
በክልሉ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ከፍተኛ ሰብአዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ስር ለማዋል እስካሁን በክልሉና በፌደራል የፀጥታ ሃይሎች በኩል በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል።
ሆኖም በክልሉ ያለው የፀጥታ መደፍረስና ጥቃት በንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በአስቸኳይ ለማስቆም የፌደራል መንግስት ከመደበኛው የህግ ማስከበር ስርአት ባሻገር በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሰረት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ በአፋጣኝ እንዲተገበር ነው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጠየቀው።
ክልሉ ወደ ቀደመ መረጋጋቱ እንዲመለስ ዜጎች ሰላማቸው ተመልሶ አርሶአደሩ ወደ እርሻው ክልሉም ወደ ልማት ስራዎች ፊቱን እንዲያዞር ለማድረግ መንግስት ያለበትን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባልም በሚል የፌደራል መንግስትን መጠየቁን ኢዜአ ዘግቧል።
በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሁለቱ አካላት መካከል ውጊያ መጀመሩን ተከትሎ በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ከነዋሪዎች አረጋግጠናል፡፡
በክልሉ ኢንተርኔት ለምን እንደተቋረጠ ኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እስካሁን ያሉት ነገር የለም፡፡