በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቻል ጋር ያደረጉትን ጨዋታ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
የመቻልን የማሸነፊያ ግብ የቀድሞ የፈረሰኞቹ ተጨዋች ከነዓን ማርክነህ በፍፁም ቅጣት ምት ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።
ፈረሰኞቹ በዛሬው ጨዋታ ሙሸነፋቸውን ተከትሎ በውድድር አመቱ ሁለተኛ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል።
የቀድሞው መከላከያ እግር ኳስ ክለብ የአሁኑ መቻል ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 33 በማድረስ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሽንፈት ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ51 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።
የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ ከተከታዩ ባህርዳር ከተማ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ጠቧል።
በቀጣይ የሊጉ መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ እንዲሁም መቻል ከ ሲዳማ ቡና እንደሚጫወቱ ከቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ጊዜ ሰሌዳ ያስረዳል።
በዘንድሮው የቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ በ51ነጥብ በአንደኝነት ሲመራ ባህርዳር በ47 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ መድህን በ41ነጥብ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ለገጣፎ ለገዳዲ እና ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በእኩል 11 ነጥብ የመጨረሻ ደረጃን ሲይዙ አርባ ምንጭ ከተማ ደግሞ 24 ነጥቦችን በመሰብሰብ የወራጅ ቀጠና ውስጥ ያሉ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ናቸው።
የኮኮብ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃን የቅዱስ ጊዮርጊሱ እስማኤል ጎሮ በ21 ጎል፣ የወልቂጤ ከተማው ጌታነህ ከበደ በ15 ጎሎች እንዲሁም የድሬድዋው ቢኒያም ጌታቸው ደግሞ በ12 ጎሎች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎችን ይዘዋል።