አቶ ግርማ የሺጥላ በምስራቅ አማራ ፋኖ መገደላቸውን የአማራ ክልል ገለጸ

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ባለፈው ሳምንት ለተገደሉት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ በምሥራቅ አማራ ፋኖ የሚመራው ‹‹ቡድን›› ነው ሲል የገለጸው ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡ 

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ባልታወቁ ግለሰቦች ግድያ እንደተፈጸመባቸው የተገለጸው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሚያዝያ 19፣ 2015 ነበር፡፡

በወቅቱ ግድያውን ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለግድያው ‹‹ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ያቃታቸው›› ያሏቸው ነገር ግን በሥም ያልጠቀሷቸውን አካላት ተጠያቂ አድርገው ነበር፡፡ አክለውም ‹‹ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ባህል በሆነበት ክፍለ ዘመን፣ በሐሳብ የተለየንን ሁሉ በጠመንጃ ለማሳመን መነሣት የጽንፈኝነት የመጨረሻው ጥግ ነው›› ብለዋል፡፡ 

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በዛሬ መግለጫው ‹‹ከሕግ የራቁ የታጠቁ ኀይሎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ እየሠራ መሆኑን›› በመግለጽ፤ የክልሉ መንግስት ከሀገር ሽማግሌዎች ከሃይማኖት አባቶች ጋር አብሮ በመስራት ‹‹ከህግ ርቀው›› ነበሩ ያላቸውን የቅማንት ታጣቂዎችን በሰላማዊ መንገድ ወደ ቀበሌያቸው እንዲገቡ ማድረጉንም ገልጧል፡፡ 

በዚህም ከጎንደር መተማ መስመር ሰላማዊ እንቅስቃሴን መፍጠር ተችሏል ያለው ቢሮው፤ በሰሜን ወሎ ዞን የሚንቀሳቀሱ የምሥራቅ አማራ ፋኖ ‹‹በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ቢያደርሱም›› አፀፋዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ‹‹በሀገሩ ባህል መሰረት በዘወልድ ሽማግሌዎች መንግስት ይቅር ብሎ›› ለሰላም እጁን በዘረጋበት ወቅት ‹‹በዚህ ኃይል የሚመራው ቡድን አመራራችን በመግደል አሁንም ህዝቡን እያሸበረ› ይገኛል ሲል አመልክቷል፡፡ 

ቢሮው በመግለጫው ይህን ቡድን ‹‹መከላከያ ሰራዊታችን ከህዝብ ለመነጠል እየሰራ የሚገኝ በመሆኑ›› አጥፊዎች ለህግ እስኪቀርቡ የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ መላው የፀጥታ መዋቅር ህዝቡ ለህግ የበላይነት መከበር ዘብ እንድትቆሙ በማለት ጥሪ አቅርቧል፡፡  የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በቡድን ታጥቆ መንቀሳቀስ በግድያና በዘረፋ የህዝቡን ሰላም የሚነሱ ላላቸው ሃይሎች ‹‹በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት እጃችሁን ከመስጠት ውጭ አማራጭ የሌለ መሆኑን አውቃችሁ እድሉን ተጠቀሙበት” ሲል ጥሪ አስተላልፏል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *