በደብረ ብርሃን መከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማዋ እንዳይገባ በሚል የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተገለጸ

ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ በሚያስኬደው ዋና መንገድ ደብረ ብርሃን ከተማ አቅራቢያ በመከላከያ እና የመንግሥትን ውሳኔ ባልተቀበሉ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ ይገኛል።

የተኩስ ልውውጡ የተጀመረው “መከላከያ ያልፋል አያልፍም” በሚል አለመግባባት መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢትዮ ነጋሪ ተናግረዋል።

ተኩሱ ከተጀመረ አንድ ሰዓት ያለፈው ሲሆን፤ የተኩስ ልውውጡ ዳሸን ቢራ ፋብሪካ አካባቢ የሚገኙ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና “ፋኖ” በመባል የሚታወቀው ታጣቂ ኃይል እና በመከላከያ መካከል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የከተማዋ እና የአካባቢው ነዋሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የአማራ ልዩ ሀይሎችን ትጥቅ ያስፈታል በሚል አዳራቸውን ሲጠብቁ እንዳደሩ እና ዛሬ ረፋድ ጀምሮ ግን የተኩስ ልውውጡ መጀመሩን ከነዋሪዎች ሰምተናል፡፡

በከተማዋ የመንግስትን እቅድ ተቃውሞ መጀመሩን ተከትሎ ትናንት እና ዛሬ የግል እና የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተዘግተዋል፡፡

መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ማደራጀት የሚል እቅድ ማውጣቱን ተከትሎ ከአማራ ክልል ህዝብ ተቃውሞ የገጠመው ቢሆንም ልዩ ሀይሎችን የማፍረስ እቅድ ሳይሆን በመከላከያ፣ በፌደራልና በክልል ፖሊስ ለማደራጀት ነው ብሏል፡፡

የመንግስትን ውሳኔ ያልተቀበሉ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት “ትጥቅ አንፈታም” በማለት ከእነ ትጥቃቸው ከካምፓቸው ወጥተዋል ተብሏል፡፡

በአማራ ክልል የፌደራል መንግስት የልዩ ሀይልን ትጥቅ የማስፈታት እቅድ ተቃውሞ ከተጀመረ ዛሬ አምስተኛ ቀኑ ላይ ሲሆን በሁሉም የክልሉ ከተሞች ህዝብ ወደ አደባባይ በመውጣት መንገዶችን የዘጉ ሲሆን ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል የሚያስኬዱ መንገዶችም ተዘግተዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *