ግዙፉ የለንደኑ ዌምብሊ ስታድዬም 90 ደቂቃ ሞልቷል የሚል ምልክት ሲያሳይ የዩናይትድ ደጋፊዎች በኩራት ስካርፋቸውን ወደሰማይ ሰቅለው አውለበለቡ።
ቀያዮቹ ሰይጣኖችና ደጋፊዎቻቸው ይህን ስሜት ካጣጣሙ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ደጋፊዎች ፊሽካው ከመነፋቱ በፊት ድላቸውን ሲያጣጥሙ፤ ይህን ለውጥ የሾፈረው ግለሰብ የአሠልጣኞች መቆሚያ ሥፍራ ላይ ሆኖ ሁኔታውን በጥሞና ይከታተላል።
ዩናይትድ ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫ ያነሳው በ2017 የአውሮፓ ሊግ ፍፃሜ ነው።
ዩናይትዶች ዋንጫውን እንዳነሱ አውቀውታል። የመጨረሻዎች ሽራፊ ደቂቃዎች ያስጨነቋቸው አይመስሉም።
በመጀመሪያው አጋማሽ በስድስት ደቂቃዎች ልዩነት አከታትለው ያስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎችን አስጠብቀው መውጣት ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው።
ምንም እንኳ በሁለተኛው አጋማሽ ኒውካስል ዩናይትድ ተነቃቅቶ ቢመጣም ኳስና መረብን ሊያገናኝ አልቻለም።
ኤሪክ ቴን ሃግ በዩናይትድ መንደር ለውጥ እያመጣ ነው ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ለዚህ ማረጋገጫ እንዲሆን ዋንጫ አንስቷል።
ዩናይትድ ዋንጫ እየጠማው ስድስት ዓመት ገደማ ሲታገል ከርሟል። አሠልጣኝ ሲሾም ሲሻር፤ ተጨዋቾች በረብጣ ብር ሲገዙ፣ ሲሸጡ ሲለወጡ ከርመዋል።
እርግጥ ነው አሠልጣኙ ዩናይትድ ከያዘ አንድ ዓመት እንኳ ባይሞላውም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ባርሴሎናን ከአውሮፓ ሊግ አሰናብተው ዋንጫ ደግሞ አንስቷል።
በማንችስተር ዩናይትድ ቤት ለውጥ እየሸተተ ነው። የዚህ ለውጥ መሪ ደግሞ ኤሪክ ቴን ሃግ ነው።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ሲጀምር ዩናይትድ ብራይተንና በብሬንትፈርድ ተሸነፈ።
ከብሬንትፈርድ ሽንፈት በኋላ ቴን ሃግ የዩናይትድ ተጫዋቾች በእረፍት ቀናቸው መጥተው 13.8 ኪሎ ሜትር እንዲሮጡ አዘዘ።
የ53 ዓመቱ ኤሪክ ተጫዋቾች ተቀላቅሎ ሩጫውን ተያያዘው።
ማንችስተር ዩናይትድ በቀጣይ ጨዋታው ሊቨርፑልን በኦልድ ትራፈርድ 2-1 አሸነፈ። ይህ ጨዋታ የዩናይትድ ጉዞ ማርሽ ቀያሪ ሆኖ ተገኘ።
ጆዜ ሞሪንሆ በመጀመሪያው ዓመት የአሠልጣኝነት ዘመናቸው ነው አሁን ካራባዎ ዋንጫ ተብሎ የሚጠራውን የሊግ ዋንጫ ያገኙት።
ሞውሪንሆ ይህን ያደረጉት የሊግ ዋንጫ ፍጻሜ ከሌሎች ዋንጫዎች ቀድሞ ስለሚመጣ ማነቃቂያ ይሆናል በማለት ነው።
ኤሪክ ቴን ሃግም ተመሳሳይ መንገድ በመከተል የሊግ ዋንጫውን በትኩረት ይዞት ይኸው ዋንጫውን ሊያነሳ ችሏል።
የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ቡድኑ ለረዥም ጊዜ ሲናፍቀው የነበረው አሠልጣኝ ተገኝቷል ብለው ያምናሉ።
አሠልጣኙ የሊግ ዋንጫን ማንሳቱ ይህን አስተሳሰብ የበለጠ ያጠናክረዋል።