በደመቀ ከበደ
በኢትዮጵያ የፈጠራና የባህል ኢኮኖሚ ላይ የተጋረጠው የ”ዲጂታል ይዘት ስርቆት” እና ችላ የመባሉ አስጊ ተፅዕኖዎች
በአዲስ አበባ እምብርት ውስጥ ወጣት የሙዚቃ አቀናባሪዎች የሙዚቃ ገበያውን ዓለም ሊያነቃንቁ የሚችሉ ቅኝቶችን ሲያመርቱ ይውላሉ። ፊልም ሰሪዎቻችን የኢትዮጵያን ማንነትና ነፍስ የሚዘክሩ ታሪኮችን በካሜራቸው ይስላሉ።
በከተማዋ በሚገኙ የሲኒማቶግራፊ ስቱዲዮዎች እና የዲጂታል አማራጮች ውስጥም የሀገር በቀል ታሪኮችን ከዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ጋር ያዋሃዱ የሚዲያ ስራዎች ለመፍጠር እየታተሩ ነው።
በሽሮ ሜዳ የእጅ ባለሙያዎችም የዘመናት ቅርስ የሆነውን የጋሞን ጥበብና ድንቅ ድሮችን ወደ ዘመናዊ ገበያ እያመጡ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ የሰርከስ ተሳታፊዎችና የውዝዋዜ ቡድኖች ጥንታዊ ትውፊትን ከዘመናዊ ፈጠራ ጋር አዋህደው ልምምዳቸውን ያደርጋሉ።
ከሶፍትዌር አልሚዎችና ዲዛይነሮች እስከ ጸሐፍትና የሶሻል ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች ድረስ የኢትዮጵያ የፈጠራ ተሰጥኦ በቀላሉ የማይጠፋና ገና ያልታለበ ታላቅ ሀብታችን መሆኑን እያሳበቁ ነው።
ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ልፋትና ትጋት ጀርባ አንድ የሚያሰጋ ጥያቄ አለ። እነዚህ “ባለሙያዎች ለደከሙበት ልፋት የሚገባቸውን ክፍያ እንዳያገኙ የፈጠራ ውጤታቸው ያለ እውቅናና ያለ ክፍያ በሌሎች እጅ የሚባክነው እስከ መቼ ነው?” የሚል።
ይህ የኢትዮጵያ የፈጠራና የባህል ኢኮኖሚ “የዝምታ ቀውስ” ነው። ዘርፉ ሙዚቃን፣ ፊልምን፣ ህትመትን፣ ፋሽንን፣ ሶፍትዌርን፣ ጌሚንግን፣ ሰርከስን፣ ውዝዋዜን፣ የእጅ ጥበብንና የሚዲያ ይዘቶችን ያጠቃልላል። በአሁኑ ወቅት ይህ ዘርፍ በዲጂታይ ይዘት ዘረፋና በዕድገት መካከል በሚገኝ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሟል።
“የብርቱካናማው ኢኮኖሚ” (The Orange Economy) ምንነት
በዓለም የቅጅና ተዛማጅ መብት ዕድገት ትንታኔ ውስጥ የኪነ ጥበብ ፈጠራና የባህል ኢኮኖሚ ብዙ ጊዜ “ብርቱካናማው ኢኮኖሚ” ተብሎ ይጠራል። ይህም የፈጠራ፣ የእውቀትና የባህል ቅርስ መገናኛ ነጥብ ነው። ብርቱካናማ ቀለም በተለምዶ ከባህልና ከፈጠራ ጋር ስለሚገናኝ እንደ ጥሬ እቃ ሳይሆን በሰው ልጅ አእምሮአዊ ብስለት ለሚመነጭ ኢኮኖሚ የተሰጠ ስያሜ ነው።
እንደ ተለመደው “አረንጓዴ ኢኮኖሚ” (ግብርና) ወይም “ቡናማ ኢኮኖሚ” (ማዕድን) ሳይሆን ብርቱካናማው ኢኮኖሚ ፈጽሞ አያልቅም። መሰረቱ ሀሳብን ወደ ባህላዊ ምርትና ጥበባዊ አገልግሎት መቀየር ሲሆን እሴቱም በቅጂ መብት (Intellectual Property – IP) ይጠበቃል።
የዓለም እና አህጉራዊ ተሞክሮዎች
በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈጠራ ኢንዱስትሪዎች ለዓለም አቀፍ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 4.73 በመቶ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ፤ ይህም እንደ ማዕድንና ሆስፒታሊቲ ካሉ ዘርፎች የላቀ ነው። የቅጂ መብትን በጥብቅ የሚከላከሉ ሀገራት ትርፉን እያፈሱት ነው።
ለምሳሌ በ2024 የዩናይትድ ኪንግደም የፈጠራ ዘርፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ 115.9 ቢሊዮን ፓውንድ አበርክቷል። ደቡብ ኮሪያ በኬ-ፖፕ (K-pop) እና በጌሚንግ ላይ ባደረገችው ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት በ2023 ብቻ 14.5 ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ አግኝታለች።
በአፍሪካም ቢሆን ባህልን ከ”መዝናኛነት” ባለፈ እንደ “ኢንዱስትሪ” የማየት አዝማሚያ ውጤት እያመጣ ነው።
ለአብነትም ኬንያ በ2026 አጋማሽ የፈጠራ ዘርፉ ለሀገሪቱ GDP 10 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ናይጄሪያ የፊልም ኢንዱስትሪው (ኖሊውድ) በየዓመቱ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኛል። ከግብርና ቀጥሎም ለዜጎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል የፈጠረ ዘርፍም ነው። ቦትስዋና እና ሞሮኮ የቅጂ መብት ላይ የተመሰረቱ ኢንዱስትሪዎች ለኢኮኖሚያቸው ከፍተኛ ደጋፊ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል።
የኢትዮጵያ ጥበባዊ እና ባህላዊ ሀብቶች
የኢትዮጵያ እምቅ አቅም ከዘመናዊው ሚዲያም በላይ ይሻገራል። እንደ ጋሞ ድር ያሉ ጥንታዊ የእጅ ጥበቦቻችን ተገቢው ጥበቃና ግብይት ከተደረገላቸው ማንነትን ከመጠበቅ ባለፈ ከፍተኛ ገቢ ያስገኛሉ። የሰርከስና የውዝዋዜ ጥበባችንም ከአትሌቲክስ ባልተናነሰ የሀገራችንን ገጽታ ለዓለም እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
ማስተዋል የሚያስፈልገው ትልቁ ነገር የቅጂ መብትን ስንጠብቅ “ጥበብን” ብቻ ሳይሆን በቢሊዮን የሚቆጠር ብር የሚያንቀሳቅሰውን ትልቅ ኢንዱስትሪ እየጠበቅን ነው። ይህም ከውጭ የሚገቡ የጥበብ ይዘቶች ላይ ያለንን ጥገኝነት በመቀነስና በሀገርኛ ይዘቶችና ጥበባዊ ስራዎች ላይ ማተኮር በከተማም ሆነ በገጠር ያለውን ማህበረሰብ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋል።
የበይነ መረብ ይዘት ምንተፋ (Digital Piracy) ዕዳ
በብዝሃ ባህልና ብዝሃ ጥበብ የታደለችው ኢትዮጵያ በ”Copyright Deficit” ወይም በቅጂ መብት ጉድለት ብዙ እሴት ነው።
ባለሙያዎችና እንደ ዩኔስኮ፣ የዓለም አዕምሯዊ ንብረት ድርጅትና መሰል ተቋማት በሚሚያሰራጯቸው መረጃዎች መሰረት በፓይረሲ (ስራን ያለፈቃድ በመቅዳትና በማሰራጨት) ምክንያት በየዓመቱ 23.8 ቢሊዮን ብር እናጣለን። ይህ ገንዘብ ከጥበብና ባህል ፈጣሪዎች፣ ከባለሙያዎችና ለሀገር ካዝና በግብር መልክ ሊገኝ የሚገባው ግን እየተሰረቀ ያለ ሀብት ነው።
አንዳንዶች “የቅጂ መብትን ማስከበር ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ዜጋ ተጠቃሚነት ይገድባል” ይላሉ። ነገር ግን የቅጂ መብት ጥበቃ ማለት ተደራሽነትን መከልከል ሳይሆን የጥበቡ ፈጣሪ ባለሙያ “የዘራው እንዲያጭድ” ማድረግ ነው። ገበሬው የዘራውን ሌላው የሚወስድበት ከሆነ የፈጠራ “መሬታችን” ድርቅ የመታው መሆኑ አይቀርም።
ከህግ ማስከበር ባለፈ የዲጂታል አማራጮች አስፈላጊነት
የዲጂታል ይዘት ስርቆት መስፋፋት አንዱ ምክንያት ስራዎችን በህጋዊ መንገድ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆን ነው። ኢትዮጵያ ህግ ከማስከበር ጎን ለጎን ዜጎች በዝቅተኛ ዋጋ ጥበባዊ ስራዎችን የሚያገኙባቸውን የሀገር ውስጥ ዲጂታል አማራጮች (Digital Platforms) ማበረታታት አለባት። ህጋዊ መንገድ ሲቀል ፈጣሪዎች የድካማቸውን ዋጋ ያገኛሉ። ለዚህም ለጥበብና ባህል ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይጀምራል።
በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን (EIPA) ከህግ አስከባሪዎች ጋር በመሆን የቅጂ መብት ምዝገባና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። የቅጅና ተዛማጅ መብቶች አዋጅም ዘመኑን በሚዋጅ መልኩና ዲጂታል ዕድሎችንና ተግዳሮቶችን ባገናዘበ መልኩ እንዲሻሻል ከባለ ድርሻዎች ጋር እየሰራ ነው።
ሰላም ኢትዮጵያ (Selam Ethiopia) በSIPRE ፕሮጀክቱ አማካኝነት ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር ባለሙያዎችንና ህብረተሰቡን ስለ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች እያስተማረ ነው።
የኢትዮጵያ ሚዲያ ምክር ቤት (EMC) ስራዎች ያለፈቃድ እንዳይሰራጩ ጥረት እያደረገ ነው። የዘርፍ ማህበራት (CMOs) በየዘርፎቻቸው መብቶቻቸው ይከበሩ ዘንድ እየተጉ ነው።
እንደ Partners Against Piracy (PAP) ያሉ የግል ዘርፍ ተሳትፎዎች (ለምሳሌ መልቲቾይስ አፍሪካ – DStv ) በአህጉር ደረጃ ባለድርሻዎችን ያሳተፈ የክትትልና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረጉ ነው።
ወደፊት የሚወሰዱ ስልታዊ እርምጃዎች
ይህንን እንቅስቃሴ ለማጠናከር የሚከተሉት እርምጃዎች መወሰድ ቢችሉ መልካም ይሆናል። ባለሥልጣኑን ማጠናከር ፡ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ህጉን ለማስፈጸም የሚያስችል በቂ በጀት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የቁጥጥር ስልጣን ሊሰጠው ይገባል።
የሮያልቲ አሰባሰብ ፡ የፈጠራ ስራ ባለቤቶች ማህበራት (CMOs) ግልጽ በሆነ መንገድ ክፍያዎችን ሰብስበው ለባለሙያው የሚያከፋፍሉበት ስርአት ሊጠናከር ይገባል።
የመንግስትና የግል ዘርፍ ትብብር፦ እንደ ሠላም ኢትዮጵያ SIPRE፣ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት እና PAP ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫና የትብብር ጥረቶች መጠናከር አለባቸው።
ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ፕላትፎርሞች፡ ዜጎች ሙዚቃና ፊልምን በረካሽ ዋጋ የሚያገኙባቸው የሀገር ውስጥ መተግበሪያዎች ሊበረታቱ ይገባል።
የጥበባት ፖሊሲ፡ የብርቱካናማው ኢኮኖሚ በሀገራዊ የልማት ፖሊሲ ውስጥ እንደ አንድ ትልቅ የሥራ ዕድል ፈጣሪ መሆኑ ዕውቅና አግኝቶ የፖሊሲ ዝግጅት መጀመሩ ይበል ያሰኛል። የፖሊሲ ትኩረት መሰጠቱ መልካም ጅምር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ፖሊሲው በባለድርሻዎች ሁሉ ሃሳብ ተሰጥቶበት በፍጥነት ሊተገበር ይገባል።
ምርጫው የእኛ ነው!
አፕሊኬሽኖችንና ድረ ገፆችን ጨምሮ በየዲጂታል ፕላትፎርሞች ( Telegram, TikTok, YouTube, Facebook እና መሰል ያለፈቃድ የሚሸጥና የሚሰራጭ እያንዳንዱ የሙዚቃ አልበም፣ የሚጋራ እያንዳንዱ የቴሌቪዥን ድራማና ፊልም፣ ያለ ሚዲያ ፈቃድ የሚሰራጭ የስፖርት ቀጥታ ስርጭቶች፣ ያለ እውቅና የሚኮረጅ እያንዳንዱ የጋሞ ጥበብ ወዘተ ማለት አንድ የጠፋ የሥራ ዕድልና የጨለመ የወደፊት ተስፋ ማለት ነው። በተቃራኒው እያንዳንዱ የሚከፈልና ህጋዊ ስርዓትን የጠበቀና ያከበረ የቅጂ መብት ክፍያ ደግሞ የኢትዮጵያንና የጥበብ ባለሙያዎችን ኢኮኖሚና ፈጠራ ያጠናክራል።
የኢትዮጵያ የፈጠራና የባህል ኢኮኖሚ የማይጠፋና ለዓለም ገበያ የሚመጥን ትልቅ አቅም አለው። ይህንን ሀብት መጠበቅ የህግ ግዴታ ብቻ ሳይሆን የሀገር ህልውና ጉዳይም ነው። ለዚህም ነው ፈጠራን እናክብር። ወጥ (ኦሪጅናልነትን) እንጠብቅ የሚባለው።