የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር መንግስት ወጪ ቅነሳ ላይ ሲሆን አሁን ደግሞ ኢምባሲዎችን ለመዝጋት ማሰባቸው ተገልጿል፡፡
ፖለቲኮ እንደዘገበው ከሆነ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የወጪ ቅነሳ አዲስ እቅድ አውጥቷል፡፡ በዚህ እቅድ መሰረትም የመስሪያ ቤቱን አመታዊ ወጪ በግማሽ በመቶ ለመቀነስ መታሰቡ ተገልጿል፡፡
እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ከቀረቡ ምክረ ሀሳቦች መካከል በዓለም ላይ ያሉ የአሜሪካ ኢምባሲዎች እና ቆንሱላ ጽህፈት ቤቶችን ለመዝጋት ታቅዷል ተብሏል፡፡
በዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኢለን መስክ ምክር የሚመራው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር መንግስት አሁን ደግሞ ትኩረቱን ወደ ኢምባሲዎች መዝጋት አዙሯል፡፡
ከቀረቡት ምክረ ሀሳቦች ውስጥ 10 የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና 17 ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን ለመዝጋት መታቀዱ ተገልጿል፡፡
በእቅድ ደረጃ እንዲዘጉ ከተባሉት ኤምባሲዎች እና ቆንሱላ ጽህፈት ቤቶች መካከል ኤርትራ፣ ግሪናዳ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሌሶቶ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሉግዘምበርግ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ጋምቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኢራቅ፣ማልታና ማልዲቭስ የሚገኙት ናቸው፡፡
እንደዘገባው ከሆነ በእነዚህ 10 አገራት የሚገኙት ኤምባሲዎች ቢዘጉም አሜሪካ ከእነዚህ አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን በጎረቤት አገራት በሚገኙ ኤምባሲዎቿ አማካኝነት ትቀጥላለች ተብሏል፡፡
ለምሳሌ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት በናይሮቢ በሚገኘው ኤምባሲዋ አማካኝነት የምታደርግ ሲሆን ከማልታ ጋር ደግሞ በጣሊያን ኤምባሲዋ ለማድረግ ማቀዷን ፖለቲኮ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
ይዘጋሉ የተባሉት ኢምባሲዎች እና ቆንሱላ ጽህፈት ቤቶች አብዛኞቹ በአውሮፓ እና አፍሪካ የሚገኙ ናቸው የተባለ ሲሆን በእስያ አንድ እንዲሁም በካሪቢያን ደግሞ አንድ ኢምባሲ ይገኛሉ፡፡
አሜሪካ በአውሮፓ ከምትዘጋቸው ቆንሱላ ጽህፈት ቤቶች መካከል በጀርመን እና ፈረንሳይ የሚገኙ ሰባት የቆንሱላ ጽህፈት ቤቶች ይገኙበታል፡፡