በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስር ተመዝግበው ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) እና ከአሜሪካ መንግስት ሌሎች ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ በመቀበል በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሲያከናውኑ የነበሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መረጃቸውን ለመንግስት እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል።
ይህ ጥሪ የአሜሪካ አስተዳደር በአገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ እያደረገ ያለውን የገንዘብ ድጋፍ መቀነስ ወይም ማቆም ጋር በተያያዘ ለቀጣይ ተግባራት አስፈላጊውን መረጃ ለመሰብሰብ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም USAIDን ጨምሮ ከማንኛውም የአሜሪካ መንግስት ተቋም የገንዘብ ድጋፍ ሲያገኙ የነበሩ ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሪፖርት እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ማህበር መንግስት በዩኤስኤይድ ጉዳይ የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቁ ይታወሳል።
ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ወደ ስልጣን የመጡት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ የረድኤት ድርጅት ወይም ዩኤስኤይድ ከአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታዎች ውጪ ሌሎች ስራዎቹን እንዳይሰራ ማገዳቸው ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ከድርጅቱ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡
በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ከዩኤስኤድ ጋር ሲሰሩ እንደነበር እና ውሳኔው ከባድ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ከ5 ሺህ በላይ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን በአባልነት የያዘው የዚህ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን እንዳሉት በዩኤስኤይድ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ከምንም በላይ ድንገተኛ መሆኑ ጉዳቱን የከፋ እንደዳደረገው ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ከሆነ በርካታ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች እየሰሯቸው የነበሩ እና ሊሰሯቸው ያቀዷቸው የሰላም፣ ጤና፣ ማህበራዊ እና ሌሎችም ስራዎች በውሳኔው ምክንያትን አስተጓጉሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እስከ 150 ሰራተኞች የነበሯቸው እና ከዩኤስኤይድ የገንዘብ ድጋፍ ሲያገኙ የነበሩ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን አሰናብተዋል የሚሉት አቶ አህመድ ውሳኔው ተጀምረው የነበሩ በርካታ ስራዎች ማስቆሙን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ተፈናቃዮችን ወደ ቤታቸው የመመለስ፣ የጤና አገልግሎቶች፣ የግጭት አፈታት ውይይቶች እና ሌሎች ስራዎች በዩኤስኤይድ ላይ በተላለፈው እገዳ ምክንያት መስተጓጎላቸውን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
አቶ አህመድ አክለውም እንደ አገር በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አማካኝነት ሊፈጸሙ ይችላሉ ተብለው መንግስት የበጀት እና ሌሎች ዝግጅቶችን ባለማድረጉ ጉዳቱ ትልቅ ነውም ብለዋል፡፡
“የበጀት መቋረጡን እንደ እድል ልንጠቀምበት የሚገባም ነገር እንዳለ እንረዳለን፡፡ ሁሌ በሰው ሀገር በጀት መመስረት አንዱ ጉዳት ይህ ነው፡፡ ከፈተና ጋር የመጣ እድል ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን” ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡
በዩኤስኤይድ ላይ የተላለፈው እገዳ ይነሳል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄም “ከዚያ ፊትም ማስተካከያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እናምናለን፡፡ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ሳይቀር የተቃወማቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ የበጀት ድጋፉን ሙሉ ለሙሉ ይቋረጣል ወይም እንደበፊቱ በተለመደው መልኩ ሊቀጥል ይችላል ብዬም አላስብም፡፡
የበጀት ድጋፉ መቀነሱ ግን እሚቀር አይመስልም፣ አብዝቶ ማቀድ ከእኛ የሚጠበቅ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል አቶ አህመድ፡፡
ጉዳዩ መንግስት የዲፕሎማሲ እና ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎችን እንዲያደርግ እንፈልጋለን ያሉት አቶ አህመድ እገዳው በግጭት ውስጥ ባለሀገር የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ቢያንስ ድጋፉ እንዲቀጥል የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡
ከአራት ዓመት በፊት በነበረው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ዘመን ኢትዮጵያ ከዋሸንግተን የምታገኛቸው የጤና ስራዎች ድጋፍ በጀት ከቀነሰባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች፡፡
እንደ አሜሪካ የውጭ እርዳታ ተቋም 2023 መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ በዓመት በዩኤስአይድ በኩል ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አግኝታለች፡፡
ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በበኩሉ ዩኤስኤአይዲ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ንብረት እንዳይሸጡ እና እንዳይለውጡ አስጠንቅቋል፡፡
ባለስልጣኑ ባወጣው መግለጫ ከእኔ እውቅ እና ፍቃድ ውጭ ንብረት ማስተላለፍ፣ ማስወገድ ወይም መሸጥ ወይም ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ እንደማይችሉ ክልከላ ተጥሎባቸዋልም ብሏል።
ማሳሰቢያውን ተላልፈው በሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል፡፡
በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ አዋጅ መሰረት የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች በማንኛውም ምክንያት ስራቸውን ካቆሙ ንብረቶቻቸውን ለመንግስት እንዲያስረክቡ ያስገድዳል፡፡