የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በአራት ክልሎች ምርጫ ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6 ኛውን ዙር ቀሪና ድጋሚ ጠቅላላ ምርጫ በሚካሄድባቸው አራት ክልሎች ምርጫ እንደሚያካሂድ ገልጿል፡፡

ምርጫ የሚካሄደው በጸጥታ እና በሌሎች ምክንያቶች ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች ነው የተባለ ሲሆን የቤንሻንጉል ጉምዝ፤ አፋር፤ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 29 የምርጫ ክልሎች ውስጥ እንደሆነም ቦርዱ አስታውቋል፡፡

በዚህ ምርጫ ፕሮግራም ለዘጠኝ የተወካዮች ምክር ቤትና ለሃያ ስድስት የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ለማካሄድ እንደታቀደም ተገልጿል፡፡

ቦርዱ ባወጣው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረትም የእጩዎች ምዝገባ ከሚያዝያ 7 እስከ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ/ም ይካሄዳል የተባለ ሲሆን የምረጡኝ ቅስቀሳ ደግሞ ከሚያዚያ 7 እስከ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ/ም ይካሄዳል፡፡

እንዲሁም የመራጮች ምዝገባ ደግሞ ከሚያዝያ 7 እስከ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ/ም ይካሄዳል የተባለ ሲሆን የድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ/ም እንደሚካሄድ ቦርዱ አስታውቋል፡፡

ቦርዱ አክሎም የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያ ይፋ የሚደረግበት ጊዜ ሰኔ 6 እና ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ/ም፣ ጊዚያዊ ውጤት በምርጫ ክልል ደረጃ ማሳወቅ ሰኔ 9 እና ሰኔ 10 2016 ዓ/ም ሲሆን የመጨረሻ እና  በቦርድ የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጊያ ጊዜ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ/ም መሆኑን ቦርዱ ይፋ አድርጓል፡፡

በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በአማራ የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ያልተካሄደ ሲሆን ክልሉ አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ በመሆኑ ምክንያት በቀሪ ምርጫ ክልሎች ምርጫው አይካሄድም ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት ምርጫ ያልተካሄደ ሲሆን ክልሉ ያካሄደው ምርጫ በቦርዱ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ምርጫ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫን ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫዎችን ያሸነፈ ሲሆን፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አምስት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ አራት፣ በኦሮሚያ የተወዳደሩ ሦስት የግል ዕጩዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንድ ዕጩ፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል የጌዴኦ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሁለት መቀመጫዎችን አግኝተው ነበር፡፡

በአጠቃላይ በሁሉም የምርጫ ክልሎች 39 ሚሊዮን መራጮች ሲመዘገቡ 847 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወቅቱ አስታውቋል፡፡

በዚህ ምርጫ አሸንፈው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ከሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መካከል አምስቱ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይሻር በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን የሶስቱ ምክር ቤት አባላት ባሳለፍነው ሳምንት ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *