የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘጠኝ ኤጲስ ቆጰሳት እንዲሾሙ ወሰነች

ላለፉት አምስት ቀናት በደዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቋል።

በጉባኤው የማጠቃለያ ፕሮግራም ችግር ባለባቸው እና አስፈላጊ በሆኑባቸው አህጉረ ስብከት 9 አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ  ውሳኔ አሳልፏል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቡነ ጴጥሮስ አክለውም “የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በሰላም እና ደስ በሚል ሁኔታ ተጠናቋል፣ ዛሬ የመጨረሻው አጀንዳ ላይ ብዙ ውይይት ተካሂዷል፣ በመጨረሻ ሁሉም አባቶች ተወያይተው ቤተክርስቲያንን የሚጠቅመው ምንድነው ? የሚለው ላይ በመምከር ውሳኔ ተላልፏል” ብለዋል።

“የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲካሄድ ተወስኗል። የመጀመሪያው ችግር ያለባቸው ሀገረ ስብከት የሚል ሲሆን ይህንን የሚያስፈጽምም 7 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል እነሱ በሚያቀርቡት ጥናት ሹመት ይካሄዳል። የሹመቱ ቀንም ወደፊት ይገለፃል። ዋናው ነገር ለቤተክርስቲያን የሚጠቅመው የትኛው ነው ? የሚለውን የጉባኤው አባላት በሙሉ ተስማምቶ ፣ በአንድ ልብ፣ በአንድ ሃሳብ፣ በመነጋገር ውሳኔ ተላልፏል” ሲሉም አክለዋል።

“የፊታችን ረቡዕ የጉባኤው ማጠቃላይ መግለጫ በቅዱስ ፓትርያኩ ይሰጣል” ያሉት አቡነ ጴጥሮስ “ብዙ የተጨነቃችሁ ምዕመናን እንዳላችሁ እናውቃለን፤ ምዕመናን በሙሉ ተጨንቃችኃል፤ አንዳንድ ጊዜ እውነት ነው ሌላ ጊዜ ወሬም ብዙ ይበዛል በዚህ ሚዲያ በበዛበት ዘመን በጣም ብዙ የተጨነቃችሁ ምዕመናን እንዳላችሁ እናውቃለን ፤ በእውነት እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ግሩም የሆነ የትምህርት ጊዜ፣ ግሩም የሆነ የውይይት ጊዜ ፣ ቤተክርስቲያን ለይተን የምትፈልገው ምንድነው የሚለውን የተወያየንበት ጊዜ ነው” ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *