በቀን 35 ሺህ ብር ይቆጥቡ የነበሩ የሿሿ ሌቦች ተያዙ

በአዲስ አበባ የ”ሿሿ ” ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተለምዶ “ሿሿ “የሚባለውን ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራውን መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።

ወንጀል ፈፃሚዎቹ ኃይል በመጠቀም ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓ/ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አንበሳ ጋራዥ አካባቢ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኦሮ 86853 ነጭ ሚኒባስ በመጠቀም ከአንድ ግለሰብ ላይ 10ሺ ብርና ግምቱ 14 ሺብር የሚያወጣ ሞባይል ስልክ ሰርቀው ይሰወራሉ፡፡

ፖሊስ ጠንካራ  ክትትል  በማድረግ ወንጀል ፈፃሚዎቹን ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር በማዋልና ምርመራ በማስፋት ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የሚፈፅሙ 14 ወንጀል ፈፃሚዎችንና  የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 ኦሮ 79184 ሚኒባስ ተሽከርካሪን ሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ /ም ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ ፋንታ ለኢዜአ አስታውቀዋል፡፡

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ግለሰቦች በቦሌ ክፍለ ከተማ 6 ቦታዎች ፣ በየካ ክፍለ ከተማ 3 ቦታዎች እንዲሁም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 3 ቦታዎች ላይ ወንጀሉን መፈፀማቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳትፎ ያላቸው 19 ወንዶችና 6 ሴቶች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሁለት ሚኒ-ባስ መኪናዎች እንዲሁም ግለሰቦቹ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚጠቀሙባቸው 4 ልዩ ልዩ ተሸከርካሪዎች ፣ 82 ሺ 680  ጥሬ ብር ፣ 14 ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ስማርት ስልኮች እና የቀን ተቀማጭ የሚያስቀምጡበት ደብተር በኤግዚቢትነት እንደተያዘ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ ፋንታ አስረድተዋል፡፡

ግለሰቦች ምንም አይነት ህጋዊ ገቢ የሚያገኙበት ስራ የሌላቸው ቢሆንም ከፍተኛው በቀን 35 ሺ ብር አነስተኛው 5ሺ ብር የቀን ተቀማጭ ሲያደርጉ እንደነበር  በኤግዚቢትነት ከተያዘው ሰነድ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ ስፍራዎች ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የተፈፀመባቸው ግለቦች አዲስ አበባ ፖሊስ  ጉለሌ ክፍለ ከተማ በመቅረብ በኤግዚቢትነት ከተያዙ ስልኮች መካከል መምረጥ እንደሚችሉ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ አስታውቀዋል፡፡

በተለምዶ ሿሿ የሚባለውን ወንጀል የሚፈፅሙ ወንጀለኞች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለው ወንጀሉን እንደሚፈፅሙና መነሻና መድረሻ የሌላቸው ሲሆኑ  ተሳፋሪውን የትነው የምትሄደው የሚል ጥያቄ እንዲሚያቀርቡ ህብተሰቡ ተገንዝቦ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *