የአፍሪካዊቷ ጋና ህግ አውጪ ምክር ቤት አባል የሆኑት አይዛክ አዶንጎ ከአንድ ዓመት በፊት የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንትን ከማንችስተሩ ተከላካይ ተጫዋች ሀሪ ማጓየር ጋር ተመሳሳይ እንደሆኑ ተናግረው ነበር፡፡
የፓርላማ አባሉ በወቅቱ “የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት እንደ ማጓየር በራሱ ላይ ግብ የሚያስቆጥር፣ ጠንካራ የስራ አጋሮቹን መትቶ የሚጥል እና እንዲቀጡ ለዳኛ አቤት የሚል ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
ግለሰቡ ይህን ንግግር ያደረጉበት ተንቀሳቃሽ ምስል በተለያዩ ማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ለብዙ ሰዎች መድረስ ችሏል፡፡
እኝህ የህግ አውጪ አባል “ስለ ማጓየር ከዚህ በፊት የተናገርኩት አስተያየት ስህተት ነበር፣ ማጓየርን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ ተጫዋቹ አሁን ላይ ምርጥ ተከላካይ መሆኑን አስመስክሯል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ለጋና ምክትል ፕሬዝዳንትን ግን ይቅርታ አልጠይቅም ያሉት እኝህ የህግ አውጪ ምክር ቤት አባል የጋና የገንዘብ አስተዳድር እና አጠቃቀም ግን አሁንም አልተስተካከለም ሲሉም አክለዋል፡፡
ጋና ብሔራዊ እዳዋ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል የተባለ ሲሆን በዛው ልክ በብድር የተገኘውን ገንዘብ አጠቃቀም ላይ ችግር እንዳለባት ይነሳል፡፡
ሀገሪቱ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም አይኤምኤፍ ተጨማሪ 3 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንድትወስድ ተፈቅዶላታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የማንችስተር ዩናይትዱ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ሀሪ ማጓየር ከደጋፊዎች እና ሌሎች ሰዎች የተጋነነ ትችቶችን ሲያስተናግድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የተጫዋቹ እናት በልጃቸው ላይ እየተደረገ ያለው የተጋነነ ተችት መሆኑን ተናግረው ልጃቸው ሁሉንም ጫና በመቋቋም የአዕምሮውን ጥንካሬ አድንቀው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ሀሪ ማጓየር በበኩሉ ከጋናዊው የቀረበለትን የይቅርታ ጥያቄ በደስታ መቀበሉን ገልጾ ትችቶች እንደሚያበረቱት ተናግሯል፡፡
በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድ ሀሪ ማጓየር ላለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ የተሸለ ብቃት በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡