የደቡብ ሱዳን የወንዶች የቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት ማጣሪያው በዚህ ዓመት በሚካሄደው የዓለም ቅርጫት ኳስ ውድድር ለመሳተፍ ማለፍ በመቻሉ ታሪክ ሰራ።
የደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ቡድን በአፍሪካ የማጣሪያ ውድድር ውስጥ ሲሳተፍ የመጀመሪያው ቢሆንም ወደ ታላቁ ውድድር በመጀመሪያ ሙከራው በማለፉ በአፍሪካ የመጀመሪያው ሆኗል።
‘ብራይት ስታር’ እየተባለ የሚጠራው ቡድኑ በግብፅ አሌክሳንድሪያ በተደረገው ውድድር ሴኔጋልን 83 ለ 75 በመርታት በሚቀጥለው ነሐሴ በሚጀመረው እና ኢንዶኖኔዢያ፣ ጃፓን እና ፊሊፒንስ በጣምራ በሚያዘጋጁት የዓለም ቅርጫት ኳስ ዋንጫ እንደሚሳተፍ አረጋግጧል።
በውድድሩ አፍሪካ በአምስት ብሔራዊ ብድን የምትወከል ሲሆን፣ አይቮሪ ኮስትም ቀደም ብላ ማለፏን አረጋግጣለች።
እንደአውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት በ2011 ከሱዳን ተለይታ ነጻ አገር ሆና የተመሠረተችው ደቡብ ሱዳን 11.5 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት አገር ስትሆን፣ በዓለም አቀፍ የቅርጫት ኳስ መድረክ ላይ መወዳደር የጀመረችው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር።
በዝነኛው የቅርጫት ኳስ ኮከብ ሉዎ ዴንግ የሚሰለጠነው የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ የቅርጫት ኳስ ቡድን ከአልጄሪያ፣ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ከግብፅ፣ ከአይቮሪ ኮስት፣ ከሴኔጋል፣ ከቱኒዚያ እና ከአንጎላ በመቀጠል ውድድሩን የተቀላቀለ 9ኛው አፍሪካዊ ቡድን ሆኗል።
“በብዙ ከሚፈተን አገር ነው የመጣነው” ሲል አስተያያቱን ለቢቢሲ ስፖርት የሰጠው አሰልጣኙ ዴንግ፣ ቅርጫት ኳስ ከሚጫወቱት “የተወሰኑት ልጆች ያለፉበት መንገድ ልትቆጣጠረው የማትችለው ነው።
“ሕይወት እየቀጠለ እንኳን ማሊያ ለብሶ መጫወት ይቅርና በርካታ ሰዎች ወደ ቤታቸው ለመመለስ ዕድል አያገኙም። ለእነሱ ከጨዋታ በላይ ነው። እጅግ ስሜት የሚነካ ነው” ብሏል።
የደቡብ ሱዳን የቅርጫር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ሴኔጋልን ካሸነፈ በኋላ ወደ ውድድሩ ለመቀላቀል ካደረጓቸው 10 ጨዋታዎች 9ኙን አሸንፏል።